በኢትዮጵዊያን ባህል ዘንድ ከጎረቤት ጋር አብሮ ከመብላትና ከመጠጣት ባለፈ ጎረቤት በልጆች አስተዳደግ ውስጥም ከፍተኛ ሚና እና ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡
ይህ ውብ ሀገር በቀል እሴት በአሁኑ ጊዜ እንዴት እንደሚታይ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ “በያገባኛል ዝግጅቱ” ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ መንክር እንደገለጹት፤ በልጅነታችን አንድ ነገር ለማድረግ ስናስብ ከወላጆቻችን በተጨማሪ የጎረቤትን ሁኔታ ግምት ውስጥ እናስገባ ነበር ምክንያቱም አላስፈላጊ ድርጊት ስንፈፅም ጎረቤቶቻችን ካዩን ይቆጡናል፣ ይገስጹናል ከዚያም ባለፈ ለቤተሰብ ስለሚናገሩብን ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ ወይዘሮ አስናቀች መንገሻ በበኩላቸው፤ ጎረቤት በልጆች አስተዳደግና የባህሪ ቀረፃ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላው አንስተው ለአብነትም የእርሳቸውን ልጆች አንድ የቅርብ ጎረቤታቸው ሲያጠፉ ተቆጥተው፣ መክረውና ገስጸው እንዳሳደጉላቸው ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግን አሁን ላይ ይህ ውብና ድንቅ ሀገር በቀል እሴት እየተሸረሸረ እንደሚገኝም አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው ይናገራሉ፡፡
ዛሬ ላይ አንድ ሰው የአንድ የጎረቤቱ ልጅ ጥፋት ሲያጠፋ ቢያይ መክሮና ገስፆ ከማስተካከል ይልቅ እንዳላዩ ማለፍና ማሽሟጠጥ እየተለመደ መጥቷል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ወላጆች ልጄን ማን ነው የነካው በማለት ጥሩ ያልሆነ አስተያየት ስለሚሰጡ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ይባስ ብሎም አሁን ላይ የጎረቤትን ልጅ ለማስተካከል መቆጣት በወላጆች በኩል የሚሰጠው ምላሽ ለስድብ አለፍ ሲልም ለክስ ሊዳርግ ስለሚችል “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም” አይነት ብሂል እያዩ እንዳላዩ ማለፍን መከተል ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ሆኖም ግን የጎረቤት ልጅን እንደ ራስ ልጅ መክሮ፣ ተቆጥቶና ገስፆ ማሳደግ ለኢትዮጵያዊ ነባር የሥነ ምግባር መገንቢያና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠውና ሊሰራበት እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ አሳስበዋል፡፡

በተለይም ይህን ውብ እሴት ወደ ነበረበት ለመመለስ ሚዲያ ህዝቡን በማስተማር በኩል የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የጎረቤትን ልጅ እንደ ራስ ልጅ መቁጠር፣ መንከባከብ መገሰጽና መምከር የኢትዮጵያዊያን ሀገር በቀል ማንነት መለያ ሆኖ ለበርካታ አመታት ተጉዟል የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰብ ትምህርት ክፍል ሀላፊና መምህር ተሾመ አበራ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ባህላዊ በሆኑ እሴቶቻችን አንድ ትልቅ ሰው የጎረቤቱን ልጅ ወይም የሰፈሩን ልጆች የእኔ ልጆች ናቸው በማለት ልጆቹ ሲያጠፉ ቢቆጣቸው ለምን ተቆጣሀቸው ተብሎ አይጠየቅም ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ህዝቡ ካለው የጠበቀ መቀራረብና ግንኙነት የመነጨ እንደሆና ተሾመ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ይህ ሀገር በቀል ባህል አሁን ላይ እየተሸረሸረ ስለሄደ እንደገና ለማስተካከል የሚያስችል ጥናት መጀመሩንና በትምህርት ስርዓቱ ለማካተት እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩም ተሾመ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
በአስማረ መኮንን
ጎረቤት በልጆች አስተዳደግ ላይ ያለዉን ሚና በተመለከተ ሃሳብዎን ያጋሩን!