በአሜሪካ ፍሎሪዳ በተካሄደው 46ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የልኡካን ቡድን ያስመዘገበው ድል በትብብር በአንድነት እና በጋራ የመስራት ውጤት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ቡድኑ አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
ለልዑክ ቡድኑ አቀባል ያደረጉት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ቡድኑ ያስመዘገበው ድል ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው 52 ሀገራት በተሳተፉበት ውድድር ላይ ከዓለም ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ በቀላሉ የተገኘ ውጤት ባለመሆኑ ኮርተንበታል ለዚህም ልዑክ ቡድኑ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል፡፡

የቡድን መሪዋ ወይዘሮ ሳራ ሀሰን በበኩላቸው በአንድነት እና በትብብር እንዲሁም በሀገራዊ ስሜት የተሰራ ስራ በመሆኑ ውጤት ማምጣት ተችሏል ብለዋል፡፡ በውድድሩ ያጋጠሙ ችግሮችን በመቋቋም ቡድኑ ለድል መብቃቱንም አንስተዋል፡፡
አትሌቶች ቀደም ብለው በትብብር እና በአንድነት መንፈስ አብረው በጋራ ልምምድ ማድረጋቸው ለተመዘገበው ድል እንዳበቃቸው አሰልጣኞች እና አትሌቶች ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል፡፡
ሰለሞን በቀለ