“ኢትዮጵያ ካየኋቸው ትልልቅ ሀገሮች አንዷ ናት” – አይሾው ስፒድ

You are currently viewing “ኢትዮጵያ ካየኋቸው ትልልቅ ሀገሮች አንዷ ናት” – አይሾው ስፒድ

AMN – ጥር 6/2018 ዓ.ም.

ታዋቂው አሜሪካዊ ዩቲዩበር እና የቀጥታ ስርጭት አቅራቢ አይሾው ስፒድ (IShowSpeed) ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ያደረገው ጉብኝት፣ የሀገርን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ የ”ሶፍት ዲፕሎማሲ” ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል። ወጣቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን ከሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች ጋር በቀጥታ ስርጭት አገናኝቷታል።

በጎዳናዎች ላይ የታየው “አርት ዲፕሎማሲ”

አይሾው ስፒድ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ የልማት ሥራዎች ባሸበረቁት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በመመላለስና ወደየንግድ ተቋማቱ ጎራ በማለት፣ በሚንኮላተፍ አንደበቱ በአማርኛና በተለያዩ ቋንቋዎች “እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ?” እያለ ሰላምታ በመለዋወጥ ለኢትዮጵያውያን ያለውን ጥልቅ ክብር አሳይቷል።

የአድዋ ድል መታሰቢያን፣ የሳይንስ ሙዚየምንና የመዲናዋን ፓርኮች የጎበኘው ወጣቱ ዩቲዩበር፣ በጥቁር ሕዝቦች ድል በመደመም የሀገሪቱን ባሕላዊ አልባሳት ለብሶ፣ ፈረስ ላይ ሆኖ የኢትዮጵያን ባንዲራ በማውለብለብ እንዲሁም ከወጣቶች ጋር የጀግንነት ባሕላዊ ጭፈራዎችን በማዜም ራሱ ተገርሞ ዓለምን አስገርሟል።

የዲጂታል መስኮትና የሕዝብ ግንኙነት

የእሱን የቀጥታ ስርጭቶች (Live Streams) በአንድ ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚከታተሉት በመሆኑ፣ መላው ዓለም በአይሾው ስፒድ የዩቲዩብ ቻናል መስኮት ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ስቋል፣ ዘፍኗል፣ ተደስቷል፤ እንዲሁም ቻናሉን በመቀላቀል አጋርነቱንና አድናቆቱን ገልጿል።

ከባሕል ጋር መተሳሰር

ወደ መርካቶ ጎራ ብሎ ፍራሽ በመሸከም የኢትዮጵያውያንን የሥራ ባሕል የተጋራው አይሾው ስፒድ፣ በቆይታው በርካታ ተግባራት በማከናወን ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን ትስስር አሳይቷል። በአንድ ቀን ቆይታው ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ተካፋይ ሆኗል፥ ወደ ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ጎራ ብሎ የገናን ባሕላዊ ጨዋታ ተጫውቷል፥ በባለሁለት እግር እንጨት (ኩትኩቶ) ላይ በመቆም፣ ቡና በመጠጣት፥ እስክስታ በመግጠም፥ ጥሬ ሥጋ በመብላት የኢትዮጵያን ባሕል ተቋድሷል።

በተጨማሪም ስኩተር በመንዳት፥ የባሕል አልባሳት መሸጫ ቦታዎች በመገኘትና ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን በመጎብኘት የመዲናዋን መንፈሳዊና ዘመናዊ ገጽታዎች ቃኝቷል።

የሰላምና የልማት ምስክርነት

የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከኢትዮጵያዊቷ ሚስ ወርልድ አፍሪካ፣ ከማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ከወጣቶች እና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት የተለያዩ ውድድሮችንና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ማራኪ ቆይታ አሳልፏል።

በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከአንደኛው የመዲናዋ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ በመንቀሳቀስ በርካታ ድርጊቶችን የከወነው አሜሪካዊው ወጣት፣ በበርካታ ሕዝብ ታጅቦ በነጻነት በመንቀሳቀስ በአዲስ አበባ ሰላምና ልማት ተደምሟል።

አስገራሚው የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር

አይሾው ስፒድ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በጣም ካስገረሙት ጉዳዮች ውስጥ ያስገረመውና ለተከታዮቹ በስፋት ያጋራው ሌላኛው ጉዳይ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ልዩነት ነው። “ጓደኞቼ አሁን ያለሁት በ2018 ዓ.ም ነው! ወደ ኋላ ተጉዣለሁ፤ ይህ አስደናቂ ነው!” በማለት ኢትዮጵያን የራሷ ካላንደር ባለቤት መሆኗን በብዙ ግርምት ነው የገለጸው። በተለይም የኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 1 ሰዓት ጀምሮ የሚቆጠር መሆኑን ለዓለም አቀፍ ተከታዮቹ ለማስረዳት ሲሞክር የነበረበት ሁኔታ የሀገሪቱን ልዩ ማንነት ለዓለም ያስተዋወቀበት ትልቅ አጋጣሚ ሆኗል።

የቡና ጉዳይ

በቆይታው የኢትዮጵያ ቡናን ሥነ-ሥርዓት የታደመው አይሾው ስፒድ፣ ቡናውን ቀምሶ “ይህ ዕውነተኛ ቡና ነው!” በማለት አድናቆቱን ገልጿል። የቡናውን መዓዛና አፈላል ሒደት በቀጥታ ስርጭት እያሳየ፣ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኗን ለሚሊዮኖች መስክሯል። የጠጣው ቡና ጠንካራ ሆኖ የፈጠረበትን የማነቃቃት ስሜትም “እንዲህ አይነት ቡና ጠጥቼ አላውቅም” በሚል ገልጾታል።

የልማትና የሰላም ምስክርነት

በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከአንደኛው የመዲናዋ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ በመንቀሳቀስ በርካታ ድርጊቶችን የከወነ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችም አጅበውት በሔደበት ሁሉ ስሙን እየጠሩ ቆይተዋል። በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ የልማት ሥራዎች ባሸበረቁት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በነጻነት ሲዘዋወር የነበረው ተጽዕኖ ፈጣሪው ወጣት፣ የአድዋ ድል መታሰቢያን፣ የሳይንስ ሙዚየምንና የመዲናዋን ፓርኮች ጎብኝቷል፤ በነጻነት መንቀሳቀሱም በአዲስ አበባ ሰላምና ልማት እንዲደመም አድርጎታል።

ከቤተ-መንግስት እስከ መርካቶ

ወደ መርካቶ ጎራ ብሎ ፍራሽ በመሸከም የኢትዮጵያውያንን የሥራ ባሕል የተጋራው አይሾው ስፒድ፣ በቆይታው ችግኝ በመትከል፣ በቤተ-መንግስት የገናን ባህላዊ ጨዋታ በመጫወት፣ በባለሁለት እግር እንጨት ላይ በመቆም፣ ጥሬ ሥጋ በመብላትና ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን በመጎብኘት ሁለንተናዊ የኢትዮጵያ ተሞክሮን ወስዷል።

የከተማዋ ግዝፈትና የሌሊት ውበት

በግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻ አናት ላይ በመቆም በአዲስ አበባ የምሽት ገጽታ የተማረከው አይሾው ስፒድ፣ በድሮን ምስል በመታገዝ ዓለም የከተማዋን ውበት እንዲመለከት አድርጓል። “ተመልከቱ፤ የኢትዮጵያ የሌሊት ሕይወት ይህንን ይመስላል፤ አስገራሚ ነው! ኦ አምላኬ! በጣም ያምራል!” ሲል አግራሞቱን ገልጿል።

በተጨማሪም “ኢትዮጵያ ካየኋቸው ትልልቅ ሀገሮች አንዷ ናት ብዬ አስባለሁ። ከኤርፖርት ተነስቼ ሆቴሌ እስክደርስ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ ፈጅቶብኛል። ከተማዋ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነች አስቡት፤ በኢትዮጵያ በጣም ተገርሜአለሁ” ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ስኬታማው ማስታወቂያ

የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከኢትዮጵያዊቷ ሚስ ወርልድ አፍሪካ እና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረገው ማራኪ ቆይታ፣ ኢትዮጵያ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ዋንኛ አጀንዳ እንድትሆን አድርጓል። ይህ ጉብኝት አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ብቻ ሳትሆን፣ ለቱሪስት የምትመችና በዲጂታል ዲፕሎማሲ ረገድ ትልቅ አቅም ያላት ከተማ መሆኗን ዳግም ያረጋገጠ ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የማኅበራዊ ሚዲያዎች ዋንኛ አጀንዳ በመሆን ከ270 ሽህ ሰዎች በላይ በቀጥታ ስርጭት እንዲከታተሉት በማድረግ አዲስ አበባ እና ኢትዮጵያን ለመላው ዓለም በቀጥታ ስርጭት አስተዋውቋል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review