በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት ታዋቂው የዩቲዩብ ይዘት አዘጋጅ ዳረን ዋትኪንስ (በቅፅል ስሙ አይሾው ስፒድ – IShowSpeed) የ”ስፒድ አፍሪካን ይጎበኛል” (Speed Does Africa) በሚል በ28 ቀናት 20 የአፍሪካ ሀገራትን የሚጎበኝበት ጉዞው አካል የሆነውን የኢትዮጵያ ቆይታውን በታላቅ ስኬት አጠናቋል።
ስፒድ በአዲስ አበባ በነበረው የአንድ ቀን ቆይታ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች የዓለም ሀገራት ካደረጋቸው ስርጭቶች ሁሉ የሚበልጥ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር እና የዲጂታል ተሳትፎ ሪከርድ በመስበር የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ የዲጂታል መድረኮች ላይ ከፍ አድርጓል።
ታሪካዊ ጉብኝትና የገጽታ ግንባታ
ይህ ጉብኝት የአፍሪካን ታሪክ፣ ባሕል እና መስሕቦች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ያለመ ሲሆን፣ ስፒድ በኢትዮጵያ ቆይታው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ በባዶ እግሩ በመጓዝ ለታሪካዊው የአድዋ ድል ያለውን ጥልቅ አክብሮት ገልጿል።
በተጨማሪም በመርካቶ ገበያ፣ በብሔራዊ ቤተ መንግስት እና በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች በመዘዋወር የኢትዮጵያን የጥሬ ሥጋ ባሕል እና ቡናን በመቅመስ ከሕዝቡ ጋር የነበረው የቀጥታ ግንኙነት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታይቶ የማይታወቅ የቀጥታ ስርጭት ዕይታን ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ እና የአይሾው ስፒድ አዳዲስ ሪከርዶች

በቀጥታ ስርጭቱ ወቅት የተመዘገቡት ቁጥሮች ኢትዮጵያን በዩቲዩብ ታሪክ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት ተርታ አሰልፏታል።
• የቀጥታ ስርጭት ተመልካቾች (Live Views)፦ በኢትዮጵያ የቀጥታ ስርጭት ወቅት በአንድ ጊዜ እስከ 270,000 የሚደርሱ ተመልካቾች የተከታተሉት ሲሆን፤ ይህም ከኬንያው (200,000) እና ከቻይናው (253,000) ሪከርድ በመብለጥ የጉብኝቱ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
በአጠቃላይ ደግሞ ስርጭቱን በዩቲዩብ ታሪክ በግለሰቦች የሞባይል ስልክ ከተደረጉ (Mobile IRL) ምርጥ 20 የቀጥታ ስርጭቶች ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።
• የዕይታ ብዛት (Total Views)፦ የኢትዮጵያው ስርጭት በተለቀቀ በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ ከ 10 ሚሊዮን በላይ ዕይታዎችን አግኝቷል። ይህም ስፒድ ቀደም ሲል በብራዚል፣ በሕንድ እና በምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ካደረጋቸው ስርጭቶች በበለጠ ፍጥነት “Trending” በመሆን ቀዳሚ ሆኗል።
• የተከታዮች ዕድገት (Subscriber Growth)፦ በኢትዮጵያ ቆይታው በነበሩት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ281 ሺህ በላይ አዳዲስ ተከታዮችን በማፍራት፣ ታሪካዊውን የ48.6 ሚሊዮን ተከታዮች ቁጥር በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሆኖ ተሻግሯል።
ይህም በዓለማችን ላይ በየቀኑ ከፍተኛ ተከታይ ከሚያፈሩት ሚስተር ቢሰትን ከመሰሉ ቁንጮ ዩቲዩበሮች ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል።
• ልዩ የተሳትፎ መጠን (Engagement Rate)፦ ቪዲዮው ከ1 ሚሊዮን በላይ ‘ላይክ’ (Likes) የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም 11% የተሳትፎ መጠን እንዳለው ያሳያል። ይህም ከዓለም አቀፉ የዩቲዩብ አማካይ ተሳትፎ (3-5%) በሁለት እጥፍ የላቀ ነው።
የአይሾው ስፒድን የኢትዮጵያ ጉዞ ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?

በዚህ ስርጭት ዩትዩበሩ ዳረን ዋትኪንስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም እንደሀገር ትልቅ ስኬትን ማስመዝገብ ችላለች። ይህንንም ስኬት ባልተለመደ ሁኔታ በታሪክ አጋጣሚ ልዩ የሚያደርጉት ሶስት ምክንያቶች አሉ።
የመጀመሪያው ተፈጥሯዊ ይዘት (Organic Growth)፦ አብዛኞቹ ከፍተኛ የሪከርድ ባለቤት የሆኑ ስርጭቶች የቦክስ ውድድሮች ወይም ትልልቅ ኩባንያዎች የሚደግፏቸው ዝግጅቶች ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያው ስርጭት ግን ያለምንም ቅድመ ማስታወቂያ እና ስፖንሰር አይሾው ስፒድ ኢትዮጵያ ተገኝቶ በመዘዋወር ብቻ የተገኘ ድል ነው።
ሁለተኛው የአልጎሪዝም ድል፦ ያለ ምንም ግዙፍ ማርኬቲንግ፣ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር እና የሕዝቡ አቀባበል የዩቲዩብን አልጎሪዝም በማሸነፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁንጮ እንዲሆን አድርጎታል።

ሶስተኛው የአዲስ አበባ ተጽዕኖ፦ ስርጭቱ በነበረባቸው ሰዓታት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲጂታል መድረኮች እንደ ቢቢሲ (BBC) እና ሲኤንኤን (CNN) ካሉ ግዙፍ ሚዲያዎች በላይ ከፍተኛ ተመልካች በማግኘት ቀዳሚ የመነጋገሪያ አጀንዳ (Global Trending Topic) ሆና ውላለች።
ለዚህ ስኬታማ ጉብኝት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን፤ እንደ አዶናይ ያሉ ታዋቂ የሀገር ውስጥ የሶሻል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም ከስፒድ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል።
በአጠቃላይ ይህ የዲጂታል ሚዲያ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም አቅም፣ የሰላም አየር እና የወጣቱን የዲጂታል ተሳትፎ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በስፋት በማስተዋወቅ አዲስ ክብረ ወሰን የተሰበረበት በመሆን ታሪክ ተሠርቷል።
በሀበነዮም ሲሳይ