በዘንድሮው የምርት ዘመን 650 ሺህ ኩንታል ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ

You are currently viewing በዘንድሮው የምርት ዘመን 650 ሺህ ኩንታል ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ

AMN-ጥር 07/2018

‎በክልሉ ኢሉባቦር ዞን ያዮ ወረዳ የጋሸቡ የቡና ዛፎችን የመጎንደል እና ከፊሎቹንም በመንቀል በአዳዲስ ችግኞች የመተካት ስራ እየተካሄደ ነው።

‎በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ እና ኢሉባቦር ዞኖች እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ እንደቀጠለ ነው።

‎በኢሉባቦር ዞን ሁሉሉ ወረዳ የሎኮ ሳያ ቀበሌ አርሶ አደሮች የአፈር እጥበት መከላከያ እርከኖችን በመስራት በክልል ደረጃ የተጀመረውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እያካሄዱ ነው።

‎በዚሁ ዞን የያዮ ወረዳ አርሶ አደሮች ደግሞ ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም በዕድሜ ብዛት የጋሸቡ እና የምርታማነታቸው መጠን የቀነሰ የቡና ዛፎችን ሲጎነድሉ እና አንዳንድ አካባቢም በአዲስ የመተካት ስራ ሲሰሩ ተመልክተናል።

‎ይህንኑ አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በክልሉ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ ቡና እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

‎ሆኖም ግን በአንዳንድ ማሳዎች ላይ ረዥም ዕድሜ በማስቆጠር የጋሸቡትን የቡና ዛፎች የመጎንደል እና በአዳዲስ ችግኞች የመተካት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የቡናን ምርታማነት ለመጨመር ትልቅ እገዛ እንደሚፈጥር በመጠቆም።

‎ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ሰፊ ስራ እየተሰራ ሲሆን በዘንድሮው የምርት ዘመን 650 ሺህ ኩንታል ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ አቅደን እየሰራን ነው ሲሉ አቶ ጌቱ ገልጸዋል።

‎የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በዞኑ የሚገኘው 60 በመቶ መሬት በቡና የተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው በአንዳንድ ማሳዎች ላይ ያለው በዕድሜ ብዛት ስለጋሸበ እና ምርት የመስጠት አቅሙ ስለቀነሰ ከግብርና ባለሙያዎች እገዛ ጋር ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም ያረጁትን የመጎንደል ወይም ሙሉ ግንዱን ዝቅ ብሎ በመቁረጥ እንደ አዲስ እንዲያቆጠቁጥ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህም የቡና ምርታማነት የበለጠ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።

‎በባለፈው አመት የምርት ዘመን 196 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንደቀረበ የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ዘንድሮም ከአምናው የበለጠ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

‎በኢሉባቦር ዞን የያዮ ወረዳ የቡና አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት በዞኑ የቡና ልማት የአርሶ አደሩ ዋነኛ መተዳደሪያ ሲሆን በመንግስት በሚደረግላቸው የስልጠና የግብዓት አቅርቦትና የባለሙያ ድጋፍ እየታገዙ ምርት የማሳደግ አቅማቸው በየጊዜው እያደገ እንደሆነ ገልጸዋል።

‎ከምርቱም የሚያገኙት ጥቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንም ነው የገለጹት።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review