ሰማይ ላይ አብራሪው፣ ምድር ላይ አልሚው፣ ካፒቴን

You are currently viewing ሰማይ ላይ አብራሪው፣ ምድር ላይ አልሚው፣ ካፒቴን

AMN- ጥር 7/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አብራሪው ካፒቴን፣ ግዙፉን አውሮፕላን በሰማይ ላይ ማብረር ብቻ ሳይሆን፣ ምድር ላይም በቴክኖሎጂ የታገዘ ድንቅ የግብርና ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ካፒቴን ሙኒር መሀመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አብራሪ ሲሆኑ፣ ሰማይ ላይ ደመናትን እየቀዘፉ ግዙፉን አውሮፕላን የማብረር ብቃት ብቻ ሳይሆን፣ ምድር ላይ ደግሞ በትንሽ ቦታ ብዙ የማምረት ጥበብን የታጠቁ ባለራዕይ ናቸው።

ካፒቴኑ ዛሬ በከተማ ግብርና ዘርፍ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን “ሃይድሮፖኒክስ” (Hydroponics) በመጠቀም ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ስራ እየሰሩ ይገኛሉ።

የካፒቴን ሙኒር የግብርና ፍቅር የጀመረው ገና ረዳት አብራሪ በነበሩበት ወቅት ወደ ሲንጋፖር ባደረጉት ጉዞ ነበር።

“ሲንጋፖር ያየሁት ነገር ቁጭትና ቅናት አሳደረብኝ” ይላሉ ካፒቴኑ።

“የመሬት እጥረት ባለበት ሀገር ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ህዝባቸውን እንዴት እንደሚመግቡ ስመለከት፣ እኛ ያለንን ሰፊ ሀብት ብንጠቀም ምን ልንሰራ እንደምንችል አሰብኩ” በማለት ወደ ስራው የገቡበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

ካፒቴን ሙኒር የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ ሃይድሮፖኒክስ (Hydroponics) ይባላል።

ይህ ዘዴ አትክልቶች ለማደግ የሚያስፈልጋቸውን ንጥረ ነገር በቀጥታ ከውሃ ጋር በማቀላቀል የሚሰጥበት እንጂ አፈር የማይፈልግ ዘመናዊ አሰራር ነው።

ቴክኖሎጂው አነስተኛ ቦታ እና ውሃ በመጠቀም በየወሩ ምርት መስጠቱ፣ ጊዜንና ጉልበትን መቆጠቡ ልዩ ያደርገዋል።

በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በዓመት አንድ ሚሊዮን ኪሎግራም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለማምረት አቅደው በቁርጠኝነት እየሰሩ ይገኛሉ።

የካፒቴን ሙኒር ትልቁ ህልማቸው፤ ለራሳቸው ገቢ ማግኘት ብቻ አይደለም።

“የእኛ ትውልድ የምግብ ዋስትናን ችግር ዛሬውኑ ሊፈታው ይገባል፤ ልጆቻችን ስለ ምግብ ዋስትና መጨነቅ የለባቸውም” ይላሉ።

ልጆቻችን ስለ ምግብ እጥረት ከማሰብ ወጥተው የዘመናቸውን የቴክኖሎጂ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ መሰረት መጣል ዋነኛ ግባቸው መሆኑን በኩራት ይገልጻሉ።

በጠባብ ቦታ፣ በትንሽ ውሃ እና በቴክኖሎጂ ታግዘን የራሳችንን ምግብ መሸፈን ብቻ ሳይሆን ለገበያም ማቅረብ እንችላለን የሚሉት ካፒቴኑ፣ ይህ ተግባር የከተማ ግብርና በኢትዮጵያ ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል በተግባር ያሳየ ታላቅ ስራ መሆኑን አመላክተዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review