ባለፉት ሰባት ዓመታት የተከናወኑ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በሀገሪቱ የነበረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት በመጠገን ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
በዛሬው ዕለት በተረካሄደው የኢትዮጵያ “የፋይናንስ እመርታ” ኮንፈረንስ ላይ የተናገሩት ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ከሰባት ዓመታት በፊት የነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተኛ መዛባት፣ የዕዳ ጫና፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የገበያ አለመረጋጋት የታየበት ነበር። መንግሥት እነዚህን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት በወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አስችሏታል።
አቶ አሕመድ ሽዴ በሪፎርሙ የመንግሥት ጠቅላላ ገቢ ከ2010 ዓ.ም ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር በ446 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን፥ በተለይም የታክስ ገቢ በ400 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ አጠቃላይ የመንግሥት ገቢ የውጭ ፍሰትን ጨምሮ በአምስት እጥፍ ማደጉን ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በአጠቃላይ 25 ቢሊየን ዶላር ከውጭ ሀብት ፍሰት ገቢ ማግኘት መቻሉና በ2010 ዓ.ም 2.5 በመቶ የነበረው የበጀት ጉድለት በ2017 ዓ.ም ወደ 0.9 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉ እንዲሁም በድህነት ተኮር ዘርፎች ላይ የሚመደበው በጀት በ2010 ዓ.ም ከነበረበት በአራት እጥፍ ማደጉን ከዋና ዋና ስኬቶቹ መካከል የሚነሱ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የመጀመሪያው እና ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ጠንካራ እና አዳዲስ ተቋማት እንዲፈጠሩ ከማድረጋቸውም በላይ፣ ቀልጣፋ የገቢ አሰባሰብ ስትራቴጂዎች እንዲነደፉ አቶ አሕመድ ሽዴ መናገራቸውን የገለጸው የተቅላይ ሚኒሰትር ጽ/ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ ነው።