በህክምናው ዓለም ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ካሉ የህክምና ዘርፎች መካከል አንዱ የጨረር ህክምና ነው። ይህ ህክምና በከፍተኛ ኃይል የሚለቀቁ ጨረሮችን በመጠቀም የካንሰር ህዋሳትን የሚገድል ወይም እድገታቸውን የሚገታ ዘመናዊ የህክምና ዘዴ ነው።
የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ክብረቅዱሳን አይነኩሉ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ህክምናው ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ምንም እንኳን የጨረር ህክምና በአብዛኛው ለካንሰር ህክምና የሚውል ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ ካንሰር ላልሆኑ እጢዎችም ሊሰጥ ይችላል። ህክምናው የሚሰጥባቸው ዋና ዋና ምክንያቶችንም ዶ/ር ክብረቅዱሳን አብራርተዋል፡፡
የጨረር ህክምና መቼ ያስፈልጋል?
• ካንሰሩን ለማጥፋት፦ ካንሰሩ ገና ሳይሰራጭ በአንድ ቦታ ላይ ብቻ ተወስኖ ሲገኝ ባለበት ለማምከን
• ለቀዶ ጥገና እንዲያመች፦ ትልልቅ እጢዎችን አሟሙቶ በማሳነስ በቀዶ ጥገና ለማውጣት እንዲያመቹ ለማድረግ
• ከቀዶ ጥገና በኋላ፦ በሰውነት ውስጥ ሊቀሩ የሚችሉ የካንሰር ህዋሳትን ለማጥፋት
• ህመምን ለመቀነስ፦ ካንሰሩ ሊድን በማይችልበት ደረጃ ላይ በሚሆንበት ጊዜ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ስቃይ ለማስታገስ የጨረር ህክምና ይሰጣል።
የህክምናው ልዩ ጥቅሞች
የጨረር ህክምና ሂደት እንደ ካንሰሩ አይነትና ደረጃ የሚለያይ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ከ10 እስከ 30 ደቂቃ ሊወስድ ይችላል። እንደ ኬሞቴራፒ መላ ሰውነትን ሳይሆን፣ ካንሰሩ ያለበትን የተወሰነ ቦታ ብቻ ለይቶ ማጥቃት ማስቻሉ ትልቁ ጥቅሙ ነው።
የጎንዮሽ ጉዳቶች
የጨረር ህክምና ጤነኛ ህዋሳት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የተለያዩ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡
• ከፍተኛ የድካም ስሜት
• የቆዳ መቆጣት፣ መቅላት ወይም መላጥ
• በራስ አካባቢ ከሆነ፦ የፀጉር መርገፍና የአፍ መድረቅ
• በሆድ አካባቢ ከሆነ፦ ማቅለሽለሽና የተቅማጥ ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ
እነዚህ የጎንዮሽ ጉዳቶች በአብዛኛው ህክምናው ካለቀ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሚጠፉ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ታካሚ ለህክምናው የሚኖረው ምላሽ የተለያየ በመሆኑ ከሀኪም ጋር በቅርበት መማከር አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ክብረቅዱሳን አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸዉ