የማይደፈር ሰማይ ፤ የማይደፈር ሉዓላዊነት

You are currently viewing የማይደፈር ሰማይ ፤ የማይደፈር ሉዓላዊነት

AMN ጥር 08/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ የማይደራደሩ ለክብሯ ደማቸውን አፍስሰዋ እሷን ያፀኑ ጀግኖች ምድር ናት።

ከእነዚህ የሀገር ምሰሶዎች መካከል ደግሞ ለዘጠኝ አስርት ዓመታት የሀገሪቱን ሰማይ እንደ ንስር እየቀዘፈ፣ እንደ አንበሳ እያገሳ ያስከበረው አየር ኃይል አንዱ ነው። የነጻነታችን ተምሳሌት፣ የሉዓላዊነታችን መከታ የአንድነታችን ምሰሶ በመሆን 90ኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ የጀግንነት እና የልዕልና ታሪክ ነው። ባለፉት 90 ዓመታት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገርን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ያልቀዘፈው ሰማይ፣ ያላካለለው አድማስና ያልሰነጠቀው ደመና የለም።

በየትኛውም የሀገሪቱ ጫፍና በየትኛውም አስቸጋሪ መልክዓ-ምድር ላይ የአየር ኃይላችን አብራሪዎች “የሀገር ሰማይ አይደፈርም” የሚለውን ቃል በደማቸውና በላባቸው አጽንተዋል።

ይህ የሃገር ኩራት የሆነው ተቋም 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ከመጪው ጥር 15 ቀን እስከ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ” የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት” በሚል ዋና መሪ ቃል በተለያዩ ኩነቶች ይከበራል።

90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስመልክቶም” የአንበሶቹ ሰማይ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ አየር ኃይል አዘጋጅነት የጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት 2026፤ የሀገራችንን ሰማይ በግርማ ሞገስ የሚያደምቅ ታላቅ ኩነት ይካሄዳል።

ይህ ትርኢት የአየር ላይ ትዕይንት የሚታይበት ብቻ

ም ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የደረሰበትን አዲስ ከፍታ እና እያደገ የመጣውን ዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት ለዓለም የሚያበስርበት መድረክ ነው፡፡

የአንበሶቹ ሰማይ የሚለው ስያሜ ዝም ብሎ የወጣ አይደለም፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች በጦር ሜዳ ያላቸውን ቁርጠኝነትና ድንቅ የበረራ ጥበባቸውን ከኢትዮጵያዊ ጀግንነታቸው ጋር የሚያስተሳስር ነው።

የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚያደርገው ደግሞ የተለያዩ ሀገራት የአየር ትርኢት ቡድኖች ጋር በጋራ የሚካሄደው የበረራ ትርኢት ነው።

ይህም ከበረራ ጥበብ ባለፈ ትልቅ የዲፕሎማሲ ትርጉም አለው። እነዚህ ሀገራት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ትርኢት ለማሳየት መምጣታቸው ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪካዊነትና ለደረሰበት የብቃት ደረጃ እውቅና መስጠታቸው ነው።

በዚህም የዘጠኝ አስርት ዓመታት የጀግንነት ታሪክን ከዛሬው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ስትራቴጂካዊ ብቃት ጋር በማዋሃድ፣ የአየር ኃይላችንን የትላንት ኩራትና የነገ ተስፋ በአንድ ላይ የሚያሳይ ሲሆን አብራሪዎቻችን በሰማይ ላይ የሚሰሯቸው አስደናቂ ትርኢቶች፣ የጀግንነት ልብ እና የጥበብ ልቅና እንዴት ተጋምደው የሀገርን ክብር እንደሚያስጠብቁ በተግባር የሚመሰክሩበት ነው።

ይህ “የአንበሶቹ ሰማይ! ኢትዮጵያ የተሰኘው ትርኢት፤ የኢትዮጵያ ሰማይ ምንጊዜም በጀግኖች ልጆቿ ጥበቃ ስር መሆኑን ዳግም የሚያረጋግጥ ፣ የአየር ኃይላችንን ክብርና ልዕልና ከከፍታ በላይ ከፍ የሚያደርግ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ይህም አየር ኃይል የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ጥምረት ብቻ ሳይሆን፤ የሀገር ፍቅር መፍለቂያ፣ የጀግንነት ማህደር እና የኢትዮጵያ ህዝብ የደህንነት ተስፋ ነው። ባለፉት 90 ዓመታት የታየው ይህ የማይለወጥ መርህ፣ ዛሬም ለነገው ትውልድ በኩራት የሚሸጋገር የታሪክ አሻራ ሆኖ ይቀጥላል። – የኢትዮጵያ አየር ኃይል

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review