39ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤንና የአፍሪካ ጣሊያን ጉባኤን አስመልክቶ ለፀጥታ አካላት ኦረንቴሽን ተሰጠ

You are currently viewing 39ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤንና የአፍሪካ ጣሊያን ጉባኤን አስመልክቶ ለፀጥታ አካላት ኦረንቴሽን ተሰጠ

AMN ጥር 8/ 2018 ዓ.ም

በቅርቡ የሚካሄደውን 39ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤንና የአፍሪካ ጣሊያን ጉባኤን አስመልክቶ ለፀጥታ አካላት ኦረንቴሽን ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር 39ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በጥብቅ ደኅንነት እና ፕሮቶኮል መምራት እንደሚያስፈልግ ገልፀው በጉባኤው ላይ ሁሉም የተሰጠውን የሥራ ድርሻ በጥብቅ ዲሲፕሊን፣ ሥርዓት ባለው አለባበስ እና የሀገርን ገፅታ መገንባት በሚያስችል መልኩ የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት መፈፀም ይኖርበታል ብለዋል።

የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን በስኬት ለማጠናቀቅ እንደመንግስት ለጉባኤው የሚመጥን ዝግጅት ተደርጓል፤ እኛም ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን፣ ሞተር ሳይክሎችንና ቴክኖሎጂዎችን ታጥቀናል ያሉት ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል እንደ ሕግ አስከባሪ ተቋማት ተቀናጅተንና ተናበን በጋራ በከፍተኛ ዲሲፕሊን በመስራት የሀገራችንን ገጽታ ከፍ በሚያደርግ መልኩ ጉባኤውን ያለ አንዳች እንከን ማሳካት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አምባሳደር ብርሀኑ ፀጋዬ በበኩላቸው ሀገራችን አሁን ላይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በፀጥታው ዘርፍ የደረሰችበትን ከፍተኛ ዕድገት ለጉባኤው ተሳታፊዎች ማስተዋወቅ እና መሸጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ የሀገራችንን መልካም ገፅታ አጉልቶ በማሳየት፣ የሀገራችንንና የቀጠናውን አሁናዊ ሁኔታን በመተንተን፣ በፀጥታው ሥራ ዜጎችን በማሳተፍ እና ኮሙዩኒኬሽናችንን በማጠናከር ሥራዎችን ያለምንም ስህተት ማከናወን አለብን ማለታቸዉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review