የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፣ ከአዲስ አበባ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ጋር በመተባበር የ2018 ዓ.ም የከተራና የጥምቀት በዓል አከባበርን በማስመልከት የተዘጋጀ የማጠቃለያ የውይይት መድረክ አካሂዷል ።
የከተራና የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በአደባባይ በድምቀት የሚከበረው በዓል ሐይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ ሁኔታ እንዲከበር የሚያስችሉ የውይይት መድረኮች ከወረዳ ጀምሮ ሲካሄዱ ቆይተዋል።
የውይይት መድረኩ ማጠቃለያም በከተማ ደረጃ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣ ሊቀጳጳሳት እንዲሁም የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ተከናውኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀኃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ በዓል መሆኑን አስታውሰው በዓሉ ሐይማኖታዊና መንፈሳዊ ስርዓቱን ጠብቆ እዲከበር ይሕን መሠል ውይይቶች የላቀ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ የስልጤና የሀዲያ ሐገረስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ ሕርያቆስ በሀገራችን ኢትዮጵያ የሠላም መንፈስ እየሰፈነ የተበታተነው እየተሳሰበ ወደ አንድነት እየመጣ ያለበት ጊዜ ነው ያሉ ሲሆን ፤ ምዕመናኑ በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የሐይማኖትና የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው የሐይማኖት ተቋማት የሰላም ምንጭና ባለቤት መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን ይሕህንኑ ሰላም ፣ አንድነትና ፍቅርን ሊሰብኩ ይገባልም ብለዋል።
በተያዘው ዓመት የመስቀል ደመራ በዓልን ጨምሮ የአእላፋት ዝማሬን የመሳሰሉ የአደባባይ ኹነቶች በሰላም መከበራቸውን የገለፁት ቢሮ ኃላፊዋ ሐይማኖታዊ ክብረበዓሉ ለሌላ እኩይ ተግባራት ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑ ባለመፍቀድ በዓሉ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የውይይቱም ተሳታፊዎችም በዓሉ የሰላም የአንድነት የፍቅር መሆኑን አንስተው በዓሉ ሐይማኖታዊ መንፈሱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ለማክበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙም አስተያየት ሰጥተዋል።
በታምሩ ደምሴ