ከብክለት ወደ ውበት

You are currently viewing ከብክለት ወደ ውበት

“በወንዝ ዳርቻ ልማቱ የከተማዋ ወንዞች ከቆሻሻ ጸድተው ለዓይን የሚማርኩ የመዝናኛ ስፍራዎች ሆነዋል”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

64 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን የታሪክ መዛግብትን ስናገላብጥ የካቲት 17 ቀን እኩለ ለሊት ላይ የተከሰተን አንድ አስከፊ አጋጣሚ እናገኛለን። ‘የሰሜን ባህር ጎርፍ’ (North Sea flood of 1962) በሚል ታሪክ ሲያስታውሰው የኖረው ይህ ክስተት የተፈጠረው በጀርመኗ ከተማ ሃምቡርግ ነበር። የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላም አሳድረን ብለው በተኙበት ያልገመቱት ነገር ገጠማቸው፡፡ የሰሜን ባህር ጎርፍ ከምዕራብ ጀርመን የባህር ዳርቻዎች ተነስቶ በሃምቡርግ ከተማ የሚገኘውን የኒደርሃፈን ወንዝን ያጥለቀለቀ ኃይለኛ ጎርፍ ተከሰተ። አደጋው የ315 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ መኖሪያ ቤቶችን ስለማውደሙ እ.ኤ.አ በ2012 በማክ ፊሊክስ በተጻፈው “የ1962 ታላቅ ጎርፍ በሃምቡርግ“ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡

በአንዲት ክፉ ቀን የተከሰተው ያ አጋጣሚ ግን በሃምቡርግ እምብርት በሚገኘው የኒደርሃፈን ወንዝ ላይ አስደናቂ ልማት ወልዷል፡፡ የከተማዋን 6 ሺህ ሕንፃዎች ያወደመው አደጋ የፈጠረው ድንጋጤ አስደናቂ የስነ-ህንፃ ጥበብ የታየበትና የሃምቡርግ ጎርፍ መከላከያን ያካተተ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ የሆነ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎችን ጭምር ፈጥሯል፡፡ ልማቱ በውስጡ ትናንሽ አምፊ ቴአትሮች፣ ሱቆች፣ ካፌዎች እና ልዩ የብስክሌት መስመሮችን ጨምሮ ሚሊዮኖች የሚዝናኑበት ቦታ ሆኗል፡፡

ልክ እንደ ሃምቡርግ ከተማ ሁሉ ደቡብ ኮሪያ በሴኡል ከተማ የሚገኘውና ለከተማ መታደስ (Urban Renewal) እንደ ትልቅ ተምሳሌት የሚጠቀሰው ታዋቂው ወንዝ ቼኦንግዬቾን (Cheonggyecheon) ወደ አስደናቂ መዝናኛነት በመቀየር በዓመት ከ18 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን ትስባለች።

ወንዙ በአንድ ወቅት በጣም ከመበከሉ የተነሳ በኮንክሪት ተሸፍኖና በላይኛው በኩል አውራ ጎዳና ተገንብቶበት ለዓመታት ተቀብሮ ቆይቷል። እ.ኤ.አ በ2003 የወቅቱ የከተማዋ ከንቲባና በኋላም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሊ ዩንግ ባክ አውራ ጎዳናውን በማፍረስ ወንዙን ወደ ቀድሞ ተፈጥሯዊ ውበቱ የመመለስ ደፋር ውሳኔ ወሰኑ። በውጤቱም ዛሬ 8 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ወንዝ የሴኡል ዋና የቱሪስት መዳረሻ፣ የህዝብ መዝናኛ እና የከተማዋን ሙቀት በመቀነስ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት የተሳካ ፕሮጀክት ሆኗል።

በእርግጥ ለመንደርደሪያ ያህል የሁለቱን ከተሞች ሁኔታ አነሳን እንጂ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በአንድ ወቅት “ባዮሎጂካዊ ሞት” ታውጆባቸው የነበሩ ወንዞች አስታዋሽ አግኝተው ለምተው ለከተሞቻቸው የኢኮኖሚ ዋልታ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ የ‘Diving into Rivers: The Complete Guide to River Health and Restoration’ መጽሐፍ ደራሲ ጣሊያናዊው ፓስኳሌ ደ ማርኮ እንደሚሉት ወንዞች ከውሃ ምንጭነት ባሻገርም በአግባቡ የልማት ስራ ከተሰራላቸው ወንዞች ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ ደራሲው ያስረዳሉ፡፡

ለአዲስ አበባም ወንዞች የመቆርቆሯ ምክንያትና የቀደመ ውበቷ መገለጫ ነበሩ። ይሁንና የአዲስ አበባ ወንዞች ለበርካታ ዓመታት የከተማዋ ‘ቆሻሻ ማጠራቀሚያ’ ተደርገው መቆየታቸው የማይካድ ሀቅ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት ወንዞቹ የፋብሪካና የቤቶች ፍሳሽ መፍሰሻ፣ የደረቅ ቆሻሻ መጣያ፣ የመጥፎ ጠረን ምንጭ ሆነው ቆይተዋል።

በወንዞቹ አካባቢ የሚያልፍ ሰው ሁሉ አፍንጫውን ይዞ የሚሮጥባቸው፣ የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹና ለበሽታ መፈልፈያ የሆኑ የቆሸሹ ስፍራዎች ነበሩ። ይህ ሁኔታ “አዲስ አበባ በወንዞቿ ትጠላለች” የሚያሰኝ መራራ እውነታን ፈጥሮ አልፏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የወንዞቹን የቀደመ ገጽታ አስመልክተው ሲናገሩ “የወንጀለኞች መሸሸጊያና የአልባሌ ተግባራት መከወኛ ሆኖ ቆይቷል” ሲሉ ይገልፁታል፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ 76 ወንዞች እንዳሉ የጠቆሙት ከንቲባዋ ወንዞቹ ከየመጸዳጃ ቤቱ ፍሳሽ የሚገባባቸው ሆነው መገኘታቸውን ነው የገለጹት።

በለውጡ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ወንዞቻችንን እናጽዳ ሸገርን እናስውብ” በሚል አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ከማድረግ ራዕይ ጋር በማስተሳሰር የወንዞች ዳርቻ ልማት መጀመሩን አስታውሰዋል ከንቲባዋ።

የወንዝ ዳርቻ ልማት በወቅቱ ለኢትዮጵያ አዲስ በመሆኑ የውጭ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ አስፈልጎ እንደነበር አመልክተዋል። ፕሮጀክቱ በተጀመረ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሆን ብቻ ልማት መከናወኑን ጠቅሰው፣ በራሳችን ሀገር በቀል አቅም ለምን አንሰራም? በሚል የዛሬ ዓመት በአዲስ መልክ ስራው መጀመሩን ጠቁመዋል። 

በኢትዮጵያውያን አቅም በስምንት ወንዞች ላይ የ47 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም የጠቆሙት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ ትልቁን ድርሻ የሚይዘውም ከእንጠጦ እስከ ፒኮክ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና መሰረተ ልማቶችን ሳይጨምር 21 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም አስታውቀዋል። በዚሁ የወንዝ ዳርቻ ውስጥ ሰባት ፓርኮች እንደሚገኙና ንግድን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደሚያብራሩት፣ ከእንጦጦ ተራሮች ተነስተው በከተማዋ በኩል አልፈው የሚጓዙና 47 ኪሎ ሜትር ርዝምት ያላቸው 8 ወንዞች ስለመልማታቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከእንጦጦ ተራራ በጉለሌ በኩል አፍሪካ ህብረት እንዲሁም ከእንጦጦ በአፍንጮ በር በባንቢስ አድርጎ አቃቂ የውሃ ማጣሪያን በሚሸፍነው ፕሮጀክት በውስጡ 28 የሚደርሱ ድልድዮች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውሃ ትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከላት ይገነቡበታል። ለእግር ጉዞና የመሮጫ ትራኮች፣ የብስክሌት መስመሮች፣ ኬብል ካር ትራንስፖርት (የገመድ ላይ መኪና)፣ መዝናኛ ግድቦች እንደዚሁም ሰው ሰራሽ ወንዞችንም ይዟል፡፡

ፕሮጀክቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ደህንነት በማሻሻልና እይታ በመለወጥ ረገድ ብዙ ሚና ከመጫወቱ በተጨማሪ፣ የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች እንዲሁም ለጎብኚዎች የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ወደ አዲስ አበባ መሳብ ያስችላል ተብሎለታል፡፡

ለከተማዋ ነዋሪ ተጨማሪ ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር፣ በወንዞች ዳርቻ እና ህዝብ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች የአገልግሎት ዘርፉን በማበረታታት ካፌዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የከተማ አስጎብኚዎችና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ማመቻቸት፤ የተፋሰስ ወንዞች ዳርቻ እና ፕሮጀክቱ ዳርቻ ያሉና ወደፊት የሚገነቡ የሪል እስቴት ፕሮጀክቶችም የዕቅዱ አካል ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ስራዎች ታዲያ ለመዲናዋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጉልበት እንደሚሰጡ መረዳት ይቻላል። ዛሬ ላይ የአዲስ አበባ ወንዞች ከቆሻሻ ጸድተው የፍሳሽ ቦይ መሆናቸው ቀርቶ፣ የህዝብ መዝናኛ፣ የቱሪስት መዳረሻና ለዓይን የሚማርኩ መዝናኛ ስፍራዎች ሆነዋል።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ፣ “በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወነው የወንዝ ዳርቻ የልማት ፕሮጀክት አቧራውን አራግፈን የደበዘዘውን ታሪካችንን እና ቅርሶቻችንን በተጨባጭ አልምተናል” ይላሉ፡፡ የወንዝ ዳርቻ ልማቱን ተከትሎ በአካባቢው ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ ጅምናዝየሞች፣ ካፍቴሪያ እና ውብ የእግረኛ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ የፈራረሱና መንገድ አልባ የነበሩ መንገዶች ተስተካክለዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች እየተከናወኑ ያሉት የወንዝ ዳርቻ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት በሰጡት አስተያየት የወንጀለኞች መደበቂያ የነበሩ ስርቻዎች ጠርተው አካባቢው ብርሃንና ውበት እንዲላበስ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በመዲናዋ የተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ የልማት ሥራዎች በመሠረተ ልማት እጦት ተራርቀው የቆዩ ነዋሪዎችን ማገናኘት መቻላቸውንም ከንቲባ አዳነች ያስረዳሉ። በመዲናዋ የተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ እና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ሲጎበኙ በሰጡት ማብራሪያ ጉለሌ ላይ ድልድይ ባለመኖሩ ህዝቡ በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ለመገናኘት ሲቸገር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ብረት እና እንጨት በማስቀመጥ በማይመች ሁኔታ ለመገናኘት ሲሞክር መቆየቱን የገለጹት ከንቲባዋ፣ አሁን ላይ ግን አካባቢውን የማስዋብ ብቻ ሳይሆን የድልድይ ግንባታ በመከናወኑ ሕዝቡን ማገናኘት የሚያስችል ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱ እየተከናወነ በሚገኝባቸው አካባቢዎች በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ማመቻቸት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ በዚሁ አንድ ዓመት ውስጥም ከወንዝ ልማቱ ባሸገር የኢሬቻ እና አራዳ ፓርኮች ተካተውበታል፡፡

ወንዞችን ማልማት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ ከ2 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በቀጥታ በወንዞች ላይ በመጠጥ ውሃ ጥገኛ ሲሆኑ፣ 25 በመቶ የዓለም የምግብ ምርት የሚቀርበውም ከወንዞች በሚገኝ ውሃ ነው። እንደዚሁም በዓመት ቢያንስ 12 ሚሊዮን ቶን ዓሳ የሚገኘው ከዚሁ ከወንዝ ነው ይላል የአሲሲዮና ገፀ ድር መረጃ፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review