“አውሮፕላን ማረፊያው አዲስ አበባ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭና ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድል ይጨምራል”
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር)
በስንታየሁ ምትኩ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓባይ ውሃ በፍትሐዊነት የመጠቀም የዘመናት ጥያቄን መልስ የሰጠውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉባ ላይ ሲመርቁ ሌላ ብስራት ይዘው ብቅ ብለው ነበር፡፡ በወቅቱ ይፋ ካደረጓቸው እና በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ከሚሰሩ የኢኮኖሚው ማርሽ ቀያሪ ፕሮጀክቶች መካከል በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የአየር ማረፊያ ግንባታ ይጠቀሳል፡፡
ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ አስጀምረዋል፡፡ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው የኢትዮጵያ የዝመና ጉዞ፣ የብልፅግና፣ የመለወጥ፣ የኢትዮጵያን ራሷን ችላ በሁለት እግሯ የመቆም መሻት የሚገልጥ ስራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ መቶ ዓመት በኩራት ከሚጠቀሱ የሰመሩ ስራዎች መካከል አንደኛውና ቀዳሚው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የተሰራው ነው፡፡ አየር መንገዱ የጥንታዊት ሀገር ምልክት፣ ኩራትና መሻት ማሳያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የመንግስታት መቀያየር፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ በውስጥና በውጭ የተደረጉ ጦርነቶችና ሌሎች ችግሮችን እየተሻገረ ብቻም ሳይሆን እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
አየር መንገዱ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የገጠሙትን ፈተናዎች በመሻገር የኢትዮጵያ ኩራት፣ የብልፅግና፣ የመሻት ማሳያ ከመሆን ባሻገር የአፍሪካ ኩራትና መመኪያ መሆን የቻለ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡ የዛሬ 80 ዓመት የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ነጻ ሳይወጡ ተመስርቶ መቆም የቻለ ኩባንያ መሆኑንም አክለዋል፡፡

አውሮፕላን ማረፊያውን መገንባት ለምን አስፈለገ?
አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ 30 በመቶ እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ባንክና የተለያዩ አበዳሪዎች ቀሪውን እንደሚሸፍኑ ይጠበቃል፡፡ በአንድ ጊዜ 270 አውሮፕላኖችን የመያዝ አቅም እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን እያስተናገደ ይገኛል። የዛሬ ሰባት ዓመት አካባቢ የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በዓመት 7 ሚሊዮን ደንበኞችን ያስተናግድ ነበር። በየዓመቱ የሚያስተናግደው ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ አኳያ ማስፋፊያ ካላደረገ ተጨማሪ ሰዎችን ማስተናገድ አይቻልም። ይህንን በመገንዘብ ለነገ ዛሬ አስቀድሞ መስራት ስለሚያስፈልግ ግንባታው ተጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንደገለፁት፣ የተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ ግምባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት በር የማድረግ ዓላማን ያነገበ ነው። የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይሆናል።
ግንባታው የሚያካትታቸው ስራዎችና ፋይዳው
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገነባበት እና በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መካከል ያለው ርቀት 38 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ ይህንን የፍጥነት መንገድ በመገንባት እንዲተሳሰር የሚደረግ ሲሆን በአንድ አቅጣጫ ስድስት፣ በሌላ አቅጣጫ ስድስት በድምሩ 12 መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ መንገድ ይገነባል። የመንገዱ አካባቢም ዙሪያውያን በአረንጓዴ እፅዋቶች የተከበበ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ እስከ ቢሾፍቱ 38 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው በሰዓት ከ120 እስከ 200 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ፈጣን የባቡር መስመር ግንባታ ይከናወናል፡፡ የባቡር መስመሩም በሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚገነባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በፈረንጆች አቆጣጠር 2030 ይመረቃል። በሁለት ምዕራፎች የሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እና ሌሎች የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲጠናቀቁ ከአስር ዓመት በኋላ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2036 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ኢኮኖሚ ትገነባለች ብለዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያው የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም የጥቂት ሀገራት አየር መንገዶች ያሳኩት ደረጃ ላይ ያደርሰዋል፤ በዓመት 110 ሚሊዮን ህዝብ ማጓጓዝ የሚችል አየር ማረፊያ ባለቤትም ያደርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ ግንባታው የተጀመረው አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በብዙ መልኩ የሚለይ ነው፡፡ የቦሌ አየር ማረፊያ 700 ሄክታር የመሬት ስፋት አለው፡፡ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ደግሞ 3 ሺህ 900 ሄክታር እንዲሁም ከአካባቢው የተነሱ ሰዎች ቦታ ሲጨመር በአጠቃላይ 5 ሺህ ሄክታር ይሸፍናል፡፡ ይህም “በአየር ላይ የሚመላለሱ መርከቦች” ወይም አውሮፕላኖችን በብቃት በማስተናገድ የኢትዮጵያን የእድገት ስብራት የሆነውን ሎጂስቲክስ መፍታት ይቻላል፡፡
አዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ በአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር አካባቢ የምትገኘው እና 1910 ሜትር ከፍታ ባላት ቢሾፍቱ ከተማ አካባቢ እየተገነባ ሲሆን ይህም ለአውሮፕላኖች ሥራ የተመቸ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ቢሾፍቱ “መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ላደረጉም ሆነ ለትራንዚት መንገደኞች ብቁ ሁኔታ ያላት ናት። ለመዲናችን ያላት ቅርበት ከነባሩ የአየር ትራንስፖርት ምኅዳር ጋር በቀላሉ የተዋሃደ አሠራር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።” ሲሉም አክለዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት በአስተዳደር፣ ድህነት እና ዘላቂ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የፖለሲ አማካሪ፣ በአፍሪካ ሰብዓዊ ኔትዎርክና የተለያዩ የጥናትና ምርምር ተቋማት ቦርድ ሰብሳቢና አባል በመሆን የሰሩት ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ አንድምታ ያለው መሆኑን አብራርተዋል። አሁን ያለው አውሮፕላን ማረፊያ የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማሟላት በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አየር መንገዶች ጭምር የሚጠቀሙበት ነው፡፡ የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲገነባ አካባቢው ገጠር የነበረ ቢሆንም በሂደት መሀል ከተማ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት አካባቢው ላይ መጨናነቅ እየተፈጠረ በመሆኑ የማስፋፊያ ግንባታ ማካሄድ አስፈልጓል፡፡
አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ድርጅቶችና የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ የአየር ማረፊያ ከተማ (Airport City) የሚገነባበት ስለሆነ ለሀገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚኖረው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ2017 በጀት ዓመት አየር መንገዱ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡ አሁን ላይ አየር መንገዱ በዓመት ከ20 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን እያገለገለ ሲሆን በአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ምክንያት 110 ሚሊዮን ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል። ይህም አቅሙን በብዙ እጥፍ በማሳደግ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው ድርሻ ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው፣ “አውሮፕላን ማረፊያው በሚገነባበት ወቅት ለስራ ተቋራጮችና ዜጎች በርካታ የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ለግንባታው የሚያገለግሉ ዕቃዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም ይገነባሉ፡፡ በዚህም ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይፈጠራል። ከዚህ ባሻገር እንዲህ ዓይነት ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲገነባ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን አገልግሎት በማቅረብ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሆቴሎች ስለሚገነቡ በርካታ የስራ ዕድሎች ይፈጠራሉ፡፡ አዲስ አበባ ላይ በርከት ያሉ ስብሰባዎች የሚደረጉበትና በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭና ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድል ይጨምራል፡፡ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መዲናነቷን ያጠናክራል፡፡ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ይጎበኛሉ” ብለዋል፡፡

ከአውሮፕላን ግንባታው ጋር ተያይዞ አዲስ አበባን ከቢሾፍቱ የሚያገናኙ ፈጣን መንገድና የባቡር መስመር መገንባቱ መንገደኞች በትራፊክ መጨናነቅ እንዳይቸገሩ ያደርጋቸዋል። የከተማዋን መሰረተ ልማት ደረጃ ያሻሽላል፡፡ በ40 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የሚኖረውን ነዋሪ የህይወት ደረጃ እንዲሻሻል በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ አጀንዳ እና የረጅም ዘመን የአቪየሽን ስትራቴጂ ጋር የተናበበ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያጠናክራል። በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ማዕቀፍ አፍሪካን የማገናኘት አቅም ይጨምራል። የንግድ እና ቱሪዝም ኮሪደሮችን ያሰፋል። ኢትዮጵያንም ቀዳሚ የበይነ አኅጉር ማዕከል እንደሚያደርጋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደተናገሩት፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው መጀመር ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለመላው አፍሪካውያን የሚያኮራ አጋጣሚ ነው፡፡ በአየር ትራንስፖርት ያለውን የመሰረተ ልማት ክፍተት በመሙላትና ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ተግባራዊነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡
አየር መንገዱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ የሚዞር፣ በአፍሪካ ሰፊ የገበያ ሽፋን ያለው የሀገርና የአፍሪካ ኩራት ነው፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባጋጠመበት ወቅት ብዙዎች አየር መንገዶች ሲከስሩና በድጎማ ሲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማ ሆኖ የቀጠለ ነው፡፡ አየር መንገዱ እንደ አንድ ትልቅ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚታይ እንደሆነ ያነሱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ግንባታው በአፍሪካ ያለውን ገበያ በማስፋት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የሚያድግበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬት ምስጢር የኮርፖሬት ባህል መገንባት መቻሉ፣ ለደህንነት ቅድሚያ መስጠቱ፣ በፈጠራና ትጋት፣ በየጊዜው ራሳቸውን ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ጋር ለማድረስ የሚጥሩ አመራሮችና ሰራተኞች ያሉት መሆኑ እንዲሁም ሁልጊዜ ለአዲስ ነገር በሩን ክፍት አድርጎ መስራቱ ነው፡፡ በጥገናና ትምህርት እያስመዘገበ ካለው ስኬት ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን ለማምረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
አየር መንገዱ ባለፉት 80 ዓመት ያሳለፈው ጉዞ የተሳካ ነበር፡፡ የሚቀጥለው 80 ዓመት ከባለፈው በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ ከደረሰንበት ዘመን አኳያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ በደንብ ካልተሰራ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ በአካልና በአዕምሮ ጠንካራ የሆነ ትውልድ ለማፍራት የቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራም በማስጀመር እና የጋራ አረንጓዴ መዝናኛ ስፍራዎችና ስታዲዬሞች በመገንባት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዓለም ሁለተኛ የሆነ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ይጀመራል፡፡ ይህም አየር መንገዱ በሚቀጥለው 80 ዓመት የሚገጥመውን አዳዲስ እውቀትና ፈተና ተቋቁሞ ለማለፍ የሚያስችለውን ብቃት እንዲጎናፀፍ እንደሚያስችለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡