የአብሮነት እሴቶችን እንዴት እናጠናክራቸው?

You are currently viewing የአብሮነት እሴቶችን እንዴት እናጠናክራቸው?
  • በጥምቀት በዓል የሚታየው መከባበር፣ መደጋገፍና መተሳሰብ የኢትዮጵያውያን አብሮነት ስር የሰደደ መሆኑን እንደሚያመላክት ተጠቁሟል

አቶ ስለሺ ደቻሳ ትውልድና እድገታቸው ካዛንቺስ ነው፡፡ ጥምቀት ሁሌም በጉጉት የሚጠብቁት በዓል እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። ከቤተሰብ፣ ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው፣ ከህዝበ ክርስቲያን ጋር በመሆን፣ ታቦታትን እያጀቡ ማክበርም ልዩ ደስታን ይፈጥርላቸዋል፡፡

እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፣ ጥምቀት የኢትዮጵያውያን አብሮነት የሚታይበት በዓል ነው፡፡ በበዓሉ የተለያየ እምነት ተከታዮች የታቦታት ስፍራዎችና መንገዶችን ማፅዳትን ጨምሮ በልዩ ልዩ መልኩ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ነው። ይህ ደግሞ መከባበርን፣ አብሮነትንና ፍቅርን ያጠናክራል፡፡

ይህንን አብሮነትና መተሳሰብ የሚያጠናክር መልካም ተግባርም በግላቸው ብቻ ሳይሆን “ፍቅር ያሸንፋል” የተሰኘ የበጎ አድራጎት ማህበር በኩል እንደሚያደርጉ አቶ ስለሺ ይናገራሉ። የማህበሩ ዋና ፀሀፊ አቶ ስለሺ እንደገለጹት፣ ይህን በበዓላት ወቅት የሚታየውን የአብሮነትና አንድነት እሴት ለማጠናከር ወጣቱን ጨምሮ ህብረተሰቡን በማስተማር የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አቶ ሚስባህ ከድር በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ነዋሪ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣ በመተሳሰብና በመረዳዳት አብረው ለዘመናት የኖሩ ህዝቦች ናቸው። እሳቸውም ከተለያየ ብሔርና እምነት ያላቸው ነዋሪዎች ጋር በመተሳሰብና በፍቅር ማደጋቸውን ይናገራሉ፡፡

የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት አቶ ሚስባህ፣ የጥምቀት በዓል ከመከበሩ አንድ ወይም ሁለት ቀን በፊት ጀለቢያቸውን ለብሰው በዓሉ ወደሚከበርበት ጃንሜዳ በመሄድ ቆሻሻ ካለ በማፅዳትና ቦታውን በማስተካከል እንደሚሳተፉ ይናገራሉ፡፡

ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመሆን “ፍቅር ያሸንፋል” የተሰኘ ማህበር ከሰባት ዓመት በፊት በመመስረት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ሚስባህ፣ እሳቸውን ጨምሮ የማህበሩ አባላት የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ወቅት አስቀድሞ በዓሉ የሚከበርበትን ቦታ በማፅዳት ለክርስትና እምነት ተከታዮች ያላቸውን ክብር፣ ፍቅርና አጋርነት ያሳያሉ፡፡ የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ሚስባህ፣ በጥምቀት በዓል ብቻ ሳይሆን በእስልምና የኢድ አልፈጥርና ኢድ አልአድሃ በዓላት ሲከበሩ እንዲሁም በኢሬቻ በዓል በተለያየ መልኩ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊ አብሮነትን የሚያጠናክር ተግባር እንደሆነና ወደፊትም እንደሚገፉበት ገልጸዋል፡፡

“ይህን በማድረጋችን በጣም ደስተኛ ነን፡፡ የምናደርገውም የክርስትና ወይም የእስልምና እምነት ተከታዮች ማፅዳት ያቅታቸዋል ብለን አይደለም፡፡ በእምነት ብንለያይም፤ ሰው ነን፤ ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በተባለች ሀገር የምንኖር ኢትዮጵያዊ ነን፡፡ የእናንተ ደስታ የእኛ ደስታ ነው” በሚል የጀመሩት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ቆሻሻን በማቃጠልና በማስወገድ ሲሳተፉ አብሮ ቆሻሻ የሆነውን አስተሳሰብ እንዲጠፋ በማድረግ አብሮነትና አንድነት እንዲጠናከር እየሰሩ እንደሆነ አቶ ሚስባህ አክለዋል፡፡

ሀምሳ አለቃ እንዳሻው የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 የኮሪያ ሰፈር ነዋሪ ናቸወ፡፡ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በበዓሉ ከመሳተፍ ባሻገር ጥር 8 እና 9 ቀን በየዓመቱ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ጃንሜዳ ለዚሁ አገልግሎት ምቹና ፅዱ እንዲሆን ማድረግ ላይ የመሳተፍ ልምድ አላቸው፡፡ “በዓሉ የሚከበርበትን ስፍራ ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በመሆን አፀዳለሁ፤ ይህንን ሳደርግ ደስታ ነው የሚሰማኝ፤ ከተለያየ እምነት ተከታዮች ጋር በመከባበር እንድንኖር፣ እርስ በርስ ያለንን ግንኙነት እንድናጠናክርም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል” ሲሉ በመሳተፋቸው የሚሰማቸውን ስሜት ይናገራሉ፡፡

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ለይኩን ብርሃኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሀዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፣ ጥምቀት በቤተ ክርስቲያኗ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ አበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ የበዓሉ ሃይማኖታዊ መነሻ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመውረድ፣ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በታላቅ ትህትና የተጠመቀበት፣ ሰው የእግዚአብሔርን ልጅነት ያገኘበት ታላቅ ምስጢር የተገለጠበት ዕለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን በገባው ቃል ኪዳን መሰረት ወደ ምድር መጥቶ የማዳን ስራውን የጀመረበት ነው።

የአከባበር ስነ ስርዓቱም መምህር ለይኩን እንደሚገልፁት፣ ጥር 10 ቀን በ“ከተራው” ዕለት በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው በመውጣት በህዝበ ክርስቲያኑ በዝማሬና እልልታ ታጅበው ከሰዓት በኋላ ባህረ ጥምቀቱ ወደተዘጋጀበት ስፍራ ይወርዳሉ፡፡ ሌሊቱም መዘምራንና ካህናት በማህሌትና በሰዓታት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፤ ስርዓተ ቅዳሴም ይከናወናል፡፡ 

ጥምቀት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ አባ አብርሃም ገብረማርያም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሀፊና በሐዋርያዊ ዘርፍ ዋና ኃላፊ፣ የጳጳሳዊ ልዑካን ማህበር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳይሬክተር ናቸው። ጥምቀት ዳግም መወለድን፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባትን፣ በእግዚአብሔር ማመንን የሚሰጥ፣ የአዲስ ህይወት መጀመር የሚገለጥበት ምስጢር ነው። በቤተ ክርስቲያኗ ጥምቀት የንስሃ መግቢያ ወይም በዓለም ከሞት ወደ ህይወትና በመንፈሳዊነት መነሳትን የሚያስገኝ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በበዓሉ ከሚከናወኑ ስነ ስርዓቶች መካከል በውሃ መረጨት አንዱ ሲሆን ይህም ጥምቀት የሚያነፃ፣ የሚያጥብ፣ ለአዕምሮ ብርሃን፣ ከክርስቶስ አዲስ ብርሃንን የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ዝግጅትና ደስታ ይከበራል፡፡ ያልተጠመቁት ይጠመቃሉ፤ የተጠመቁት ደግሞ የመጀመሪያ የጥምቀት ቀናቸውን እያሰቡ መንፈሳዊ ህይወታቸውን እና እምነታቸውን ያድሳሉ፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ነጭና ያማረ ልብስ ለብሰው ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፤ ከቤተሰብ፣ ጎረቤትና ማህበረሰብ አብረው ያሳለፉትን የደስታ ጊዜ እያሰቡ፣ በአብሮነትና በደስታ እንደሚያከብሩ አክለዋል፡፡

የአብሮነት ተምሳሌት

ጥምቀት ኢትዮጵያውያን “የጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ…” በሚለው ብሂል አምረውና ደምቀው የሚታዩበት በዓል ነው፡፡ የተለያየ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል ያላቸው ሰዎች በራሳቸው ቀለም ኮርተው፣ ተውበውና ደምቀው ይታያሉ። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂና አንትሮፖሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ዶዳ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ በጥምቀት በዓል በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል የሚታየው መከባበር፣ መደጋገፍና መተሳሰብ የኢትዮጵያውያን አብሮነት ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ልዩ ልዩ የቋንቋና የባህል ማንነት ያላቸው ሰዎች በጋራ በዓልን ማክበር በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነትና ውበት ያሳያል።

ከበዓሉ በፊትም በአዲስ አበባ ከተማ ዋናው ጥምቀተ ባህሩ የሚከናወንበትን ቦታ በማፅዳትና በማዘጋጀት የእስልምና እና የተለያየ እምነት ተከታዮች መሳተፍ ከሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ድንበሮች የዘለለ የመከባበር እና የመተባበር እሴት ትልቅ ማሳያ ነው። የጋራ ሰብአዊነት እና  ግቦች ከግለሰባዊ ልዩነቶች የበለጠ ጉልህ እንደሆኑ ያስተምረናል፡፡ በብዝሃ ማህበረሰብ ውስጥ በሰላም አብሮ የመኖር እድልን ያጎላል ይላሉ፤ ዘሪሁን (ዶ/ር)።

የማህበረሰብ ልማት ልዩ ባለሙያ አቶ ዘላለም ይትባረክ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ “የአደባባይ በዓላት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አላቸው። በዓላቱ የበዓሉ ባለቤት ብቻ ሳይሆኑ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ሀብቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡-

የጥምቀት በዓል የእምነቱ ተከታዮች ብቻም ሳይሆን የሀገርና የዓለም ሀብት ነው፡፡ ኢኮኖሚን በማነቃቃት፣ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ በማስቻልና የሀገርን መልካም ገፅታ በመገንባት ትልቅ ሚና አለው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የጥምቀት በዓል ሲከበር የእስልምና እምነት ተከታዮች ጎዳናዎችን፣ የታቦታት ማደሪያዎችን በማፅዳት፣ ታቦታት የሚያልፉበት ቦታ በመልቀቅ ጭምር ድጋፍ ሲያደርጉና ሲሳተፉ ይታያል፡፡ በዚህ ብቻም ሳይሆን በሌሎች በዓላትም የሚታየው ይህ አይነቱ መተሳሰብ፣ አብሮነትና መደጋገፍ ለማህበረሰብና ሀገር እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው መስራት እንደሚገባ አቶ ዘላለም ይናገራሉ፡፡

ዘሪሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በበዓሉ ዝግጅት እና አከባበር ወቅት የተለያየ ማንነት ያላቸው ሰዎች አብረው ሲመገቡ፣ ሲዘፍኑ እና ሲጨፍሩ ማየት በህዝቦች መካከል ያለውን ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስርና መስተጋብር የሚያሳይ ነው። ሰዎች በጋራ የአምልኮ ሥርዓቶች እና በዓላት ላይ እንዲሰባሰቡ እድል ይሰጣሉ። የባለቤትነት ስሜትን እና የጋራ ማንነትን ያጠናክራሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ላለ ህብረ ብሔራዊ ሀገር እንደነዚህ አይነት በዓላት እንደ መከባበር፣ ልግስና እና ሰላም ያሉ የጋራ እሴቶችን የሚያጎሉ በመሆናቸው በባህል መካከል ውይይት እና የጋራ መግባባትን ያበረታታሉ። በተጨማሪም እነዚህ ክስተቶች ብዙውን ጊዜ የበጎ አድራጎት ተግባራትን እና የጋራ ድጋፍን ያካትታሉ፣ ለምሳሌ ምግብን ለድሆች ማጋራት ወይም ማጽዳት እንዲሁም የህዝብ ቦታዎችን ማዘጋጀት፣ ይህም በሰዎች መካከል መተማመንን እና አብሮነትን እንደሚፈጥሩ ያስረዳሉ፡፡

 በበዓላት ቀናት ከሚታየው ባሻገር

እንደ ጥምቀት ባሉ በዓላት የሚታዩትን የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች ከበዓላት ባሻገር ቀጣይነት እንዲኖራቸው የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ወሳኝ እንደሆነ የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ዘላለም ይናገራሉ፡፡ “ለምን ብናኝ አታክልም፤ እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን መወጣት ከቻልን በዓልን ተገን አድርገን የምናሳያቸው በጎ ባህሎች ሀገራዊና ተቋማዊ ይዘት እንዲኖራቸው ከማስቻል አኳያ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው” ይላሉ፡፡

የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ዘላለም እንደሚናገሩት፣ እያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን ኃላፊነት መወጣት ከቻልን እንደሀገርም ሆነ ማህበረሰብ የችግር ጊዜያችን ማሳጠር ይቻላል። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የተለያዩ ችግሮች አሉብን፡፡ ችግሮቻችንን ይፈታሉ ብለን የምናምንባቸው ምግባሮች ወይም እሴቶች በእለት ተለት ሕይወታችን የምንጠቀምባቸውና ዘላቂ እንዲሆኑ ኃላፊነትን መውጣትና ምላሽ መስጠት አለብን፡፡

እንደ ጥምቀት ባሉ በዓላት ላይ የሚታዩትን የአንድነት እና አብሮነት እሴቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ ባህሎች እና ወጎች አስተምህሮዎች ማካተትና ማስተማር እንደሚገባ  ዘሪሁን (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡

ሌላው የሃይማኖቶች እና የባህል ውይይቶችን ማበረታታት ያስፈልጋል። የተደራጁ መድረኮች እና ከተለያየ አስተዳደግ የተውጣጡ ሰዎችን የሚያቀራርቡ ዝግጅቶች፣ በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና ጭፍን ጥላቻን ለመቀነስ ይረዳል።

የማህበረሰብ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ መተግበርም ሌላው በህዝቦች መካከል አንድነትን፣ መረዳዳትና አብሮነትን ለማጠናከር ያግዛል፡፡ የጋራ ጥረት እና የድጋፍ መንፈስን ለማስቀጠል እንደ የጽዳት ዘመቻዎች ወይም የበጎ አድራጎት ዝግጅቶች ያሉ የትብብር ተነሳሽነቶች በመደበኛነት መደራጀት እንዳለባቸው ዘሪሁን (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡

ዘሪሁን (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፣ መገናኛ ብዙሃንም አንድነትን፣ መረዳዳትና አብሮነትን በማጎልበት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህ ረገድም የሚዲያ ተቋማት የአብሮነት እና የአንድነት ታሪኮችን ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ፤ ሌሎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እነዚህን ልማዶች እንዲኮርጁ በማነሳሳት ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

በየደረጃው ያሉ መሪዎችም ማህበረሰቡ ሀይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶቻቸውን በተግባራቸው እና በመልእክቶቻቸው በንቃት ማስተዋወቅ እና አርአያ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህም በበዓላት ወቅት የተመሰከረው የአንድነት መንፈስ ቀጣይ እና የህብረተሰብ ህይወት ወሳኝ አካል እንዲሆን እንደሚያስችል ነው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ዘሪሁን (ዶ/ር) የሚያስረዱት፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ትህትናን፣ ፍቅርን፣ ከምንም በላይ የራቁትን ማቅረብ፣ የወደቁትን ማንሳትን ነው ያስተማረን ያሉት መምህር ለይኩን፣ የራቀን ሰው ካለ ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ሰውን ከውድቀት እንዳወጣውና ከፍ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ክብር ልንሰጥ፣ ፍቅርና አንድነታችንም ልናጠናክር ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

አባ አብርሃም በበኩላቸው፣ የተለያየ እምነት የምንከተል ብንሆንም እግዚአብሔር የፈጠረን ሰዎች መሆናችን አንድ ያደርገናል፡፡ የጥምቀት በዓል ሁሉም በመንፈስም፤ በስጋም አብሮ በማክበር የሚደሰትበት፣ አንድነቱን የሚገልፅበትና ኢትዮጵያዊነት የሚታይበት በዓል ነው፡፡ እነዚህን መልካም የሆኑ እሴቶች ከበዓል ባሻገር በዕለት ተለት ህይወት ማሳየት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በበዓላት የሚታየውን የአብሮነትና አንድነት እሴት ለማስቀጠል፣ የአንዱ መኖር ለሌላው መኖርና ማደግ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ፣ አብሮነታችንን ለማጠናከር መስራት ይኖርብናል፡፡ አብሮነትን ለመሸርሸር የሚመጣ ሲኖር ደግሞ በጋራ መታገል እንደሚገባ አቶ ሚስባህ ተናግረዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review