ጥምቀት እና ሽሮ ሜዳ

You are currently viewing ጥምቀት እና ሽሮ ሜዳ

በሽሮ ሜዳ አካባቢ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ምክንያት ሱቆችና በውስጣቸው ያሉ ምርቶች በግልፅ የመታየት እድል በማግኘታቸው የንግድ ስራው መነቃቃቱ ተጠቁሟል

ጥምቀት እንደገና! የመወለድ ድንቅ ምስጢር ነው፡፡ ኃይማኖታዊ ትርጓሜው ከነ ታላቅ ክብሩ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ ነብር ዥንጉርጉር የሆነው ቀይ፣ ጠይም፣ ጥቁር እና የቀይዳማው መልካችን በቀለማት ባሸበርቁና በሀገር ልጆች በእነዚያ የማር እጆች በተሸመኑት አልባሳት እንደ ሌት ጨረቃ ግርዶሹን ገፍፎ ይታያል፡፡ በሰሞነ ጥምቀት ሁሉም በባህል ልብሱና ጌጣጌጡ ተውቦ ወደ አደባባይ ይወጣል፡፡

በተለይ አዲስ አበባ እንደ ፅጌሬዳ ፈክታ ከምትታይባቸው የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው፤ ጥምቀት፡፡ በሀገር ልጆች ተሸምነው የቀረቡ የባህል አልባሳትን የተጎናፀፉ የመዲናዋ ነዋሪዎች በተዋቡት ጎዳናዎች ላይ ሽር ብትን ሲሉ ላስተዋለ ሰው አንዳች የውበት ፏፏቴ ከእንጦጦ ተራራ ስር ፈልቆ በውቦቹ የመዲናዋ ጎዳናዎች የፈሰሰ ያህል ይሰማዋል፡፡

በርግጥም ይህንን ሁሉ ወፈ ሰማይ ከባህሉ አስታርቀው እንደ ንጋት ጀምበር ያስዋቡ እጆች ያሉትም እንጦጦ መዳረሻ ሽሮ ሜዳ ላይ ነው፡፡ አዎ! በህብረ ቀለማት የተሸቆጠቆጠው የሽሮ ሜዳ ገበያ በጥምቀት ሰሞን በውበት ላይ ውበትን ደርቦ ይደምቃል፡፡ ይፈካል፡፡ ይዋባል፡፡ ያስውባል፡፡

የመዲናዋ የውበት ምርኮኞች፣ የባህል አርበኞች እና ከራሳቸው የተወዳጁ የበዓሉ ታዳሚዎች ከአዘቦት ቀን በዛ ብለው ወደ ሽሮሜዳ ያመራሉ፡፡ ከዚህ ሰፊ የባህል ሙዚየም ቀልባቸው የወደደውን እና አቅማቸው የፈቀደውን ሸምተው በጥምቀት እንደ ባዘቶ ጥጥ ፈክተው፣ እንደ በጋ ፀሐይ ደምቀው፣ እንደ ንጋት ኮከብም ተውበው ይታያሉ፡፡

‘ሽሮ ሜዳ ወይ እንጦጦ፣

መቼ ቀረ ልቤ ቆርጦ፡፡’ እንዳለች ዘፋኟ፣ በኮሪደር ልማት ዳግም የተወለደችውን ሽሮ ሜዳን ያየ ሰው ልቡ ቆርጦ አይቀርም። ምክንያቱም በሽሮ ሜዳ ኢትዮጵያ በራስ ጥበብ ደምቃ ትታያለችና፡፡ አዎ! ወደ ሽሮ ሜዳ መሄድ ወደ እራስ መቅረብ፤ ከራስም መታረቅ ነው፡፡

ይህንን ፅሑፍ ለማሰናዳት ወደ ስፍራው ባቀናንበት ወቅት የኮሪደር ልማቱ ባመጣው በረከት በእንዝርት መልክ በተሰሩት ውብ መናፈሻዎች ዘና እያለ ያገኘነው ወጣት ታሪኩ ደምሌ እንደሚለው ወደዚህ አካባቢ ሲመጣ በትዝታ ፈረስ ወደ ትውልድ ስፍራው ድንገት ይነጉዳል፡፡ አንዳንዴ የወዳጅ ዘመድ ናፍቆትን አስረስቶ ፈገግ ያሰኘዋል። ደግሞም ይመልሰውና ለሰመመን አስረክቦት ይሄዳል፡፡ ቢሆንም ሽሮ ሜዳ ለሱ መልኩን እንደሚያይበት መስታወት ናት፡፡ ከዓመታት በፊትም ያደንቃት የነበረችው ሽሮ ሜዳ በኮሪደር ልማት የበለጠ በመዋቧ የእሱን ብቻ ሳይሆን የብዙዎችን ደስታ ከፍ ስለማድረጉም አጫውቶናል፡፡

የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዘሪሁን እሸቱ (ዶ/ር) አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት እንደመስቀል ወፍ እያየናት ተለውጣለች፡፡ ደምቃለች፡፡ ተውባለች፡፡ ከስሟ ትርጓሜ ጋርም እየተጣጣመች መጥታለች፡፡ ከመንገዶቿ፣ ከወንዝ ዳርቻ፣ ከህንፃዎቿና መሰል ልማቶቿ ባሻገርም የማህበራዊ መስተጋብራችንን የሚያጣፍጡ፣ ሰውን ከተፈጥሮ፣ ሰውን ከሰው፣ ሰውን ከራሱ፣ ሰውን ከባህሉ የሚያስታርቁ ስራዎችም ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

ለአብነትም ሽሮ ሜዳና አካባቢውን የጠቀሱት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አካባቢው በኢትዮጵያውያን ሀገር በቀል ዕውቀት የተሰሩ አልባሳት፣ የሸክላ ውጤቶች የሚገኙበት ነው፡፡ በመሆኑም ስፍራው ከንግድ ባሻገር ህብረ ብሔራዊነታችን ከፍ ብሎ የሚታይበት ነው፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያውያን ውብ አልባሳት በራስ እጅ ተሸምነው የሚቀርቡበትን ይህንን ስፍራ በኮሪደር ልማት ከነ ሙሉ ክብሩ ከፍ አድርጎ ማልማት ተችሏል፡፡

እንዲህ አይነት ስፍራዎችን በዚህ መልኩ ማልማት ማለት ትርጉሙ ከፍ ያለ መሆኑን የጠቀሱት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዘሪሁን (ዶ/ር) ሰው ከባህሉ እንዲወዳጅ፣ አንዱ ባንዱ ባህል እንዲያጌጥና እንዲኮራ በማድረግ ማህበራዊ ትስስራችንን ያጎለብታሉ፡፡ ሀገራዊ አንድነታችንንም ያጠናክራሉ፡፡ ለአብነትም በጥምቀትና መሰል የአደባባይ ለዓላት ለምናየው ውበትና አብሮነት የሽሮ ሜዳ አይነት አካባቢዎች አበርክቶ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ  አቶ ወልዴ ወገሴ እንደሚሉት የኮሪደር ልማቱ ያመጣውን በረከት ተከትሎ 800 ዘመናዊ ሱቆች በሽሮሜዳና አካባቢው ተገንብተዋል፡፡  ለ 2 ሺህ ወጣቶችም የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡ 1 ሺህ 500 ሰው የሚይዝ ሞል ለሽመና ባለሙያዎች ተገንብቷል፡፡ ክፍለ ከተማው በሽመናና በሸክላ ስራ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን እና አካባቢውንም የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የጥምቀት በዓልና የሽሮ ሜዳ ሀገር በቀል አልባሳት ገበያ የማይነጣጠል ቁርኝት አላቸው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ግዛው ማሞ በተለይ ደግሞ የኮሪደር ልማቱ በሽያጭ ሂደትና በደንበኞች ፍሰት ያመጣው ለውጥ ቀላል እንዳልሆነ መታዘባቸውን ነግረውናል፡፡

እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቀደም ሲል አካባቢው የተጨናነቀ በመሆኑ ለገበያ የቀረቡ ምርቶችን በግልፅ ለማየት ያስቸግር ነበር፡፡ አሁን ግን በኮሪደር ልማቱ መንገዶቹ ሰፍተዋል፡፡ የመሸጫ ሱቆቹም በውስጣቸው ያሉ ምርቶችን በግልፅ የሚያሳዩና ውብ  ሆነዋል፡፡

ከዚህ ባሻገርም በምሽትም እንደልብ ሊያሰሩ የሚችሉ የጎዳና ላይ መብራቶች፣ ሰፋፊ የተሸከርካሪና እግረኛ መንገዶች፣ ምቹ የመኪና ማቆሚያዎች እና መሰል ልማቶች በአካባቢው በመከናወናቸው የንግድ ልውውጡን የተቀላጠፈ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ የቱሪስቶችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ እንደፈለጉ የሚንቀሳቀሱበት፣ የአካባቢውን ውብ ገፅታ በፎቶ ካሚራቸው ብቻ ሳይሆን በአርበ ልቦናቸው የሚያስቀምጡበትን ዕድልም ይፈጥራል ብለዋል፡፡

“ዛሬ ሽሮ ሜዳ እንደ በባህል ልብሶቻችን ተውባለች” ስትል ሀሳቧን ያጋራችን እና በአካባቢው በሀገር ልብስ ንግድ ስራ የተሰማራችው ወለላ እጅጉ አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት ማራኪ ገፅታን ተላብሳለች፡፡ በተለይ ደግሞ ሽሮ ሜዳ ላይ የታየው ለውጥ የሚገርም ነው፡፡ የአካባቢውን የቀደመ መታወቂያ ሳይለቅ ግን ደግሞ መንገዶች ሰፍተውና የተለያዩ መናፈሻዎች ተጨምረው ከመገንባታቸው ባሻገር ለሽያጭ ያቀረብናቸው የሀገር ባህል ልብሶቻችን በአግባቡ ተሰድረው በግልፅ መታየት በሚችሉበት ሁኔታ መሸጥ የምንችልባቸው ዘመናዊ ሱቆች በመገንባታቸው የገዥዎችን ትኩረት መሳብ ተችሏል፡፡ በዚህም ከበፊቱ የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ አለ፡፡ የጥምቀት በዓልን ተከትሎም ወደ ሽሮ ሜዳ ለጉብኝትም፣ ለመግዛትም የሚመጣው ሰው ቁጥርም መጨመሩን እንደታዘበችም ነግራናለች፡፡

የዝግጅት ክፍላችን በቀንና በማታ ባደረገው ምልከታ የሽሮ ሜዳ አካባቢ የቀድሞ ወዝና ለዛውን ጠብቆ አዲስ ውበትን ተጎናፅፎ ይታያል፡፡ ሽሮ ሜዳ፣ ማታ እንደጨረቃ ፈክታ፤ ቀን እንደ ፀሐይ ደምቃ መታየት ጀምራለች፡፡ በተለይም የጥምቀት በዓልን ተከትሎ ልክ እንደ መርካቶ የንግድ እንቅስቃሴው ጦፏል። በርግጥም ሽሮ ሜዳ ከጫጉላ ቤት እንደወጣች ሙሽራ ፊቷ ወዝቷል፡፡ አዲስ አበቤዎች ደግሞ በጥምቀት በዓል ከሽሮ ሜዳ በሸመቱት የሀገር ልብስ ተውበው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እንደ ከዋክብት አምረው ይታያሉ፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review