• የባህል ልብስ ኢንዱስትሪው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር እንደ ጥምቀት ያሉ ሕዝባዊ በዓላት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተጠቁሟል
“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ!” የሚለው የቆየ ብሂል ኢትዮጵያውያን ለበዓሉ ያላቸውን ክብር ብቻ ሳይሆን፣ አልባሳት ለማኅበራዊ መስተጋብራቸው ያላቸውን ከፍተኛ ቦታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ጥምቀት ኃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ባሕላዊ የፋሽን ትርኢት በአደባባይ የሚታይበት ታላቅ መድረክ ነው። ህጻናት፣ ወጣቶችና በእድሜ ከፍ ያሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጥምቀትን አንድም ይባረኩበታል፤ አንድም መስክ ላይ ፈክቶና አብቦ እንደሚታየው የጥቅምት አበባ አደባባዮቹን በውብ የባህል አልባሳት ደምቀው ይታዩበታል፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም የእነዚህን አልባሳት፣ ውበት፣ ዲዛይንና ቀለም ከሥነ ጥበብ አንጻር በጨረፍታ እንደሚከተለው ዳስሶታል፡፡
ውበት፣ ቀለምና የባህል አልባሳት በጥምቀት ሰሞን
በኢትዮጵያ ምድር ጥር 11 ቀን ሲመጣ አየሩ ሁሉ ይቀየራል። የከተራው ዋዜማ ጭብጨባና ዕልልታ፣ የታቦታቱ ጉዞ፣ የካህናቱ ያሬዳዊ ዝማሬ እና ሕዝቡ በባህል አልባሳት አጊጦ በአደባባይ መንቀሳቀሱ ሀገሪቱን በልዩ መንፈስ ይሞላታል። ከዚህ አንጻር ጥምቀት ለኢትዮጵያውያን ኃይማኖታዊ ሥነ- ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ በላቀ መልኩ ብሔራዊ ማንነት የሚታደስበት፣ ማኅበራዊ ትስስር የሚጸናበት እና የሥነ ጥበብ ክህሎት በአደባባይ የሚመሰከርበት ታላቅ ማህበራዊ በዓል ነው።
ጥምቀት በክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የትውስታ ማህደራቸው ላይ ግዙፍ ቦታ የያዘ ታላቅ በዓል ነው፡፡ ምንም እንኳን በዓሉ ኃይማኖታዊ ዳራ ያለው ቢሆንም፣ እሱን ተከትሎ ተግባራዊ የሚደረጉ ባህላዊ ክዋኔዎች የበለጠ ድምቀት አጎናጽፈውታል፡፡ ሀገራችን ባህለ-ብዙ መሆኗን በሚገልጽ አኳኋን እንደየአካባቢው ወግና ልማድ ኃይማኖታዊ ዳራውን ሳይለቅ በዓሉ በድምቀት ይከበራል፡፡
ምንም እንኳን የጥምቀት አከባበር ለጎልማሶችና ለአዛውንቶች ታላቅ ትዝታ የያዘ ቢሆንም፤ ለህጻናትና ለወጣቶች ደግሞ ዛሬ ላይ እየተደሰቱ የሚኖሩት እጅግ ተናፋቂ በዓል ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል፤ እጅግ አዳዲስ ትዕይንቶችንና ክዋኔዎችን በማከል የጥምቀት በዓል አከባበር ዛሬም እምር ብሎ በአደባባይ መከበሩን የቀጠለው፡፡ በተለይ በህብረ-ቀለማት የአሸበረቁ አልባሳት ለብሰው የሚታዩ ወጣቶችና ሌሎች የበዓሉ አክባሪዎች የበዓል ትዕይንቱን ይበልጥ ተናፋቂ ያደርገዋል፡፡
ራሄል አበራ ተወልዳ ያደገችው ጥቁር አንበሳ አካባቢ ነው፡፡ ይህ አካባቢ የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አጫውታናለች፡፡ የጎላ ሚካኤል ታቦትን አጅባ ብዙ ጥምቀቶችን አክብራለች፡፡ አሁን ላይ የምትኖረው ፈረንሳይ ሌጋሲዮን ኬላ የሚባል አካባቢ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከአንዱ በስተቀር አራቱን የጥምቀት በዓል ያከበረችው ተከራይታ በምትኖርበት ፈረንሳይ ሰፈር ነው፡፡ ራሄል የጥምቀት በዓልና የባህል አልባሳትን በሚመለከት ተሞክሮዋን ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል አጋርታለች፡፡ ራሄል በአስተያየቷ፣ “ጥምቀት ማህበራዊ መስተጋብር የሚያጠናክር፣ ለልጆችና ለወጣቶች ትልቅ ነጻነትና ደስታ የሚሰጥ በዓል ነው። ልጅ ሆኜ ጥምቀትን በአዲስ ልብስ ነበር የማከብረው፡፡ አባቴ ለእኔና ለወንድሞቼ ለጥምቀት አዲስ ልብስ ይገዛልን ነበር፡፡ በበዓሉ አዲስ ልብስ የመልበስ አዝማሚያ ዛሬም እንደቀጠለ ነው” ብላለች፡፡
ራሄል የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ለማክበር አዲስ ልብስ አሰፍታለች። ከቅርብ ሴት ጓደኛዋ ጋር በመሆን ነው ልብሱን አስቀድመው ያሰፉት። የባህል አልባሳት ዲዛይን እጅግ መሻሻሉን ያነሳችው ራሄል፣ “ዋጋው ግን ትንሽ እየተወደደ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ጥምቀት ያለ ባህላዊ አልባሳት የሚደምቅ አይመስለኝም፡፡ ከልጅነታችን ጋር የተያያዘ ስለሆነ በጥምቀት በዓል አዲስ ዲዛይን የተደረገ ልብስ ማሰራቷን” መቼም እንደማታቆም ተናግራለች፡፡ ለጥምቀት የማሰራቸው ልብሶች ጥምቀት ካለፈ በኋላም እንደምለብሳቸው ታሳቢ በማድረግ ነው ዲዛይን የማደርገው፡፡ በተለይ የሳምንቱ ዕረፍት ቀናትና ሌሎች የበዓል ቀናትም ስለምለብሳቸው፣ ለዚህ የማወጣው ወጪ ያን ያህል አያሳስበኝም ብላለች፡፡
በእርግጥ የጥምቀት በዓል ፋይዳ ከአዳዲስ አልባሳት ያለፈ ትልቅ ሀገራዊ ዕሴታችን ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ትልቁ ማኅበራዊ ፋይዳው መሰባሰብ ነው። በዘመናዊው ዓለም ግለኝነት (Individualism) እየነገሰ በመጣበት ወቅት፣ በጥምቀት ግን በርካታ ሰዎች በአንድ እንዲሰባሰቡ ያደርጋል፡፡ ሁሉም በነጭ ባሕላዊ ልብስ ተውቦ፣ በአንድነትና በነጻነት ይሳተፋል። በአደባባይ የሚከበረው ይህ በዓል የማኅበራዊ መደብ ልዩነት የማይስተዋልበት በመሆኑ ሀገራዊ ፋይዳው ትልቅ ነው፡፡
የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል የጥምቀት በዓል አከባበርና የባህል አልባሳት መልክና ገጽታን በሚመለከት ዲዛይነርና የባህል አልባሳት የሚሰራው ፀጋዬ ስሜነህን አነጋግሯል፡፡ ዲዛይነር ፀጋዬ ለዓመታት የባህል አልባሳት ሰሪ፣ ዲዛይነርና ሻጭ ነው፡፡ መርካቶ ሸማ ተራ ውስጥ ለዓመታት የባህል አልባሳት ሰርቷል፡፡ አሁን ላይ ቀጨኔ መድሐኒዓለም አካባቢ የባህል አልባሳት ዲዛይን ያደርጋል፡፡ ዲዛይን ያደረጋቸውን ልብሶች በመስራት ለለባሽ ብቻ ሳይሆን የባህል አልባሳት ለሚሸጡ ሰዎች ጭምር ይሸጣል፡፡
ዲዛይነር ጸጋዬ ስለ ጉዳዩ በሰጠው አስተያየት፣ “በጥምቀት ዕለት የሚለበሱት አልባሳት ተራ ጨርቆች አይደሉም። እያንዳንዱ ጥልፍ፣ ጥበብ እና ዲዛይን የአንድን ማኅበረሰብ ታሪክና ጥበብ ይተርካል። ወጣቶች፣ አዛውንቶችና ሕፃናት እንደ አካባቢያቸው ባህል ለብሰው ጥምቀትን ለማክበር ወደ አደባባይ ሲወጡ፣ ሀገሪቱ በአንድ ጊዜ የፋሽን ሳምንት እያከበረች ይመስላል። በየዓመቱ የጥምቀት በዓል ላይ በአደባባዩ የሚታየውም ይኸው ትዕይንት ነው ብሏል፡፡
የጥምቀት በዓል ለዲዛይነሮችና ለሀገር ባህል አልባሳት ሰሪዎች ትልቅ የደንበኛ ማፍሪያና የፈጠራ ማሳያ ነው የሚለው ዲዛይነር ጸጋዬ፣ አዳዲስ የጥበብ ቅርፆች የሚታዩትና የሕዝቡን ቀልብ የሚስቡት በዚህ ወቅት ነው። ይህም የባሕል ልብስ ኢንዱስትሪው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር እንደ ጥምቀት ያሉ ሕዝባዊ በዓላት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አጫውቶናል፡፡
ጥምቀትን ተከትሎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቡድንና በተናጠል በመሆን የሀገር ባህል አልባሳት ለብሶ መታየት እየተለመደ መምጣቱን በማስታወስ፤ በዚህ ልክ ተወዳጅ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምክንያት ምንድ ነው? ሲል የዝግጅት ክፍላችን ላቀረበለት ጥያቄ ዲዛይነር ፀጋዬ ሲመልስ፣ “የባህል አልባሳት በብዛት ተፈላጊነታቸው የሚጨምረው ለጥምቀት በዓል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች በዓላትም ላይ የባህል አልባሳት የበዓል አድማቂዎች ናቸው፡፡ እኔም ለበዓላት በቋሚነት ልብስ የምሰራላቸው ደንበኞች አሉኝ። ደንበኞቼ በዓል በመጣ ቁጥር ትልቁ ፍላጎታቸው ከዚህ ቀደም ያልተለመደ አዲስ አይነት የባህል አልባሳት ዲዛይን እንዳደርግላቸውና እንድሰራላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ነው የባህል አልባሳት ገበያ ላለፉት ዓመታት ሞቅ ደመቅ እንዲል ምክንያት የሆነው” ብሏል፡፡
ዲዛይነር ጸጋዬ እንዳጫወተን፣ የጥምቀት አልባሳት መሠረታቸው የ“እጅ ጥበብ” ነው። በኢትዮጵያ ባሕላዊ አልባሳት ውስጥ “ጥበብ” የሚለው ቃል ሁለት ትርጉም አለው፤ አንደኛው የልብሱ ጠርዝ ላይ የሚሠራው ያሸበረቀ ዲዛይን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የባለሙያው ክህሎት ነው። በቀደመው ዘመን የጥምቀት ልብሶች በዋናነት የሚሰፉት ከነጭ የጥጥ ድርና ማግ ነበር። ይህ ነጭነት የመንፈሳዊ ንጽህና እና የደስታ ምልክት ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር ዲዛይነር ጸጋዬ አጫውቶናል፡፡
በጥምቀት በዓል ወቅት የሚታዩ ቀለማት በዘፈቀደ የሚመረጡ አይደሉም የሚለው ጸጋዬ፣ እያንዳንዱ ቀለም የራሱ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ ለምሳሌ ነጭ ቀለም በበዓሉ ጎልቶ የሚታይ ቀለም ነው። ይሄ ነጭ ቀለም ንጽህናን፣ ሰላምንና ብርሃንን ይወክላል። ወርቃማና ቢጫ ቀለሞችም የበዓሉ ሌላኛው መገለጫ ናቸው፡፡ በባህላዊ አልባሳት ዲዛይኖች ውስጥ ወርቃማና ቢጫ ቀለሞች መጠቀም የባለቤቱን ማኅበራዊ ደረጃና የክብረ በዓሉን ታላቅነት ያሳያል ብሏል።
የባህል አልባሳት ለዝነጣ እንዲመቹና ዘመኑን እንዲመስሉ ተደርገው ዲዛይን መደረጋቸው በተለይ የወጣቱ ፍላጎት እንዲጨምር እንዳደረገ የሚናገረው ዲዛይነር ፀጋዬ፣ በዚህ ላይ ወጣ ያለና ሰው እንደፍላጎቱ የሚሆንለትን የባህል አልባሳት ለማሰራት እድል ስለፈጠረለት አልባሳቱን ይበልጥ ተመራጭ አድርጓቸዋል። በሰርግና በመልስ ጊዜ ሳይቀር የባህል አልባሳት እየተመረጡ ናቸው፡፡ ይህም ሀገራዊ እውቀትና የግለሰቡ ጥረት ከተጣመሩ ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮቻችንን ለማዘመንና ዘመኑን እንዲዋጁ ለማድረግ ጥሩ ማሳያዎች እንደሆኑ አጫውቶናል፡፡
በአጠቃላይ የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ስርዓቱ ባለፈ በውስጡ የያዘው ማኅበራዊ እሴት ወደር የለውም። የዕምነቱ ተከታዮች አጊጠውና ተውበው በአደባባይ መታየታቸው በራስ ባሕል መኩራትና ለህዝባዊ አንድነት መጠናከር የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ጥምቀት የኢትዮጵያዊነት ድምቀት፣ የእደ ጥበብ መፍለቂያና የአብሮነት ማሳያ ሆኖ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ እዚህ ድረስ መምጣቱ የበዓሉ ታላቅ ዕሴትነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በአብርሃም ገብሬ