አዕምሮን የሚያድሱ መናፈሻዎች

You are currently viewing አዕምሮን የሚያድሱ መናፈሻዎች

በአዲስ አበባ 126 ፓርኮች አሉ ፤ ከእነዚህ ውስጥ 104ቱ ኮሪደር ልማቱ ያስገኛቸው አዳዲስ መናፈሻዎች ናቸው

ኮሪደር ልማቱ መልካም አጋጣሚን ከፈጠረላቸው መካከል ፓርኮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አዳዲስ ፓርኮች ቁጥራቸው እንዲበራከት ከማድረግ ባለፈ ነባሮችን ወቅቱን በሚመጥን መልኩ የማልማት ስራ ውጤቱ በተጨባጭ እየታየ መሆኑን አምባሳደር ፓርክን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ “የአዲስ አበባ ወንዞች ትንሳኤ” በሚል ርዕስ በተሰራው ዘጋቢ ፊልም ላይ ይኸንኑ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከተማን እንደ አዲስ መስራት ብቻ ሳይሆን ነባሮቹንም ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲሄዱ አድርጎ ማደስና የተበላሸውን ማስተካከል፣ የጎደለውን ማፅዳትና መሙላት እንደሚቻል አምባሳደር ፓርክ በማሳያነት እንደሚጠቀስ ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡  

“አምባሳደር ፓርክ የቁርጡሚ እና የቀጨኔ ወንዞች ቆሻሻ ይዘው እየመጡ ሰው እንዳይጠቀምበት አድርገውት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ወንዞቹ የራሳቸው ማጣሪያ አላቸው፡፡ ፓርኩም ታድሷል ብቻ ሳይሆን እንደ አዲስ ተገንብቷል። አንዱ እንምጣበት ተብሎ የሚጓጓበት ትልልቅና የሚያማምሩ ዛፎች ጭምር ያሉበት ነው” በማለት ነዋሪዎች ፓርኩን እንዲጎበኙት፣ እንዲዝናኑበትም ጭምር ጋብዘዋል፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ወደ ስፍራው በማቅናት ምልከታ አድርጎል እና ሰዎችንም አነጋግሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መሰል ፓርኮችን በማበራከት ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት አነጋግሯል፡፡ 

ወጣት ሽኩር ባቲን በአምባሳደር ፓርክ የመግቢያ ገንዘብ ተቀባይ ነው። በፓርኩ ከአንድ ዓመት በላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ፓርኩ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ከመታደሱ በፊት የነበረው ገፅታ “ለመዝናናት የማይመች፣ ቆሻሻ ወንዝ ያለበት ነበር፡፡ ፋውንቴኑ ቢኖርም አገልግሎት አይሰጥም ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ ጥሩ ነገር ለማየትና ለመዝናናት  ከፍለው የሚገቡ ሰዎች እንደጠበቁት ስለማይሆንላቸው ተበሳጭተው ይወጣሉ፡፡ የልጆች መጫወቻ እንዲሁም ለዓይን የሚስብ አበባና ሳር ያልነበረውና ማረፊያ ወንበሮቹን አዕዋፋት ያቆሸሹት ነበር፡፡ ንፁህና በቂ መፀዳጃ ቤትም አልነበረውም፡፡ በአጠቃላይ ለመዝናናትም ሆነ አዕምሮን ለማሳረፍ ምቹ ሳይሆን ቆይቷል” ሲል ገልጾታል፡፡  

“አምባሳደር ፓርክ እድሳት ከተደረገለት በኋላ ሳቢና ማራኪ ሆኗል። ከዚህ በፊት ያልነበሩ ማረፊያ ወንበሮች፣ የልጆች መጫወቻዎች፣ መፀዳጃ ቤት፣ አበባና ለምለም ሳር… ተሟልተውለታል፡፡ የሚዝናኑ ሰዎችም እንደ በፊቱ ተሳድበው ሳይሆን ተደስተውና አመስግነው ነው የሚወጡት፡፡ በፊት እንደገቡ ወዲያውኑ ነበር ተመልሰው የሚወጡት፤ በአሁኑ ወቅት ግን ጠዋት ከገቡ እስከ ማታ ድረስ ነው የሚቆዩት፡፡ የግቢው ፅዳት፣ የውሃ አገልግሎቱ በአጠቃላይ ምቹ በመሆኑ እኛም ገንዘብ የምናስከፍለው አንገታችንን ሳንደፋ በደስታ ነው” ሲል እድሳቱ ለተገልጋዮችም ሆነ ለፓርኩ ሰራተኞች ምቹ መሆኑን ነግሮናል፡፡  

ወጣት ምህረት ወጣንም ያገኘናት በፓርኩ በዛፉ ጥላ ስር በተመስጦ ተቀምጣ ራሷን ስታዳምጥ ነው፡፡ ፓርኩ ከመታደሱ በፊትም ለመዝናናት ትመጣ ነበር፡፡ የቀደመ ገጽታውን ከአሁኑ ጋር በማነጻጸር ስትገልጽም፣ “ምቹ ያልነበረና ንፅህናውም ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ፀሐዩም ያስቸግራል፡፡ ውስጥ ላይ እንድንቆይ የሚስብ ነገር አልነበረም” ስትል ታስታውሳለች፡፡ በአሁኑ ወቅት  መፀዳጃ ቤቱ፣ ማረፊያ ወንበሮቹ፣ አበቦቹ፣ ሳሩ ቀልብን ይስባሉ፡፡ በስራ ሲደክመኝና ሃሳብ ሲበዛብኝ በዚህ ቦታ መጥቼ የጥሞና ጊዜ አሳልፋለሁ፡፡ አንዳንዴ ከጎደኞቹ ጋር የመምጣት ልምድም አለኝ፡፡ በነፋሻማ አየሩ የአዕምሮ ሰላም አገኛለሁ፡፡ የኮሪደር ልማቱ እና እድሳቱ ተዳምረው ለአካባቢው ውበትን አላብሰውታል፡፡ በዚህም ወደ ፓርኩ በመምጣቴ ተዝናንቼና ደስተኛ ሆኘ እመለሳለሁ” ብላለች፡፡

የሰባት ዓመት ህፃን ልጃቸውን ይዘው እየተጓዙ ፓርኩ ውስጥ ያለውን ፋውንቴን ሲያሳዩት ያገኘናቸው ደግሞ አቶ ያሲን አብዲ ናቸው፡፡ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህጻን ልጃቸውን ሊያሳክሙ ከክፍለ ሀገር መምጣታቸውን ነገሩን፡፡ “ለየት ያለ ነገር ተመልክቻሁ፤ አየሩ፣ የአይን ማረፊያ የሆኑት ዛፎቹና ሳሩ በዚሁ ውለን ብናድር የሚሰለቹ አይደሉም፡፡ በህክምና ተቋሙ የነበረውን ጭንቀት እና መሰል ውጥረቶች በዚህ ተወግዶልኛል፡፡ ልጄም ደስታው ወደር የለውም፡፡ በሌላ ቦታ ብዙ ገንዘብ ከማውጣት በትንሽ ብር መዝናናትና መደሰት የሚቻልበት ቦታ ነው” ብለዋል፡፡  

“መዝናናት ብዙውን ጊዜ በስራችንና በህይወታችን የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም ይረዳል፡፡ በዚህም ከመጣሁበት አካባቢ እንዲህ አይነት ቦታዎች ቢኖሩ ብዬ ተመኘሁ” ሲሉም  አቶ ያሲን አክለዋል፡፡  

ወይዘሮ ቤተልሔም አበራ የአምባሳደር ፓርክ ማናጀር ናቸው፡፡ የአምባሳደር መናፈሻ በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ከታደሰ በኋላ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት  በተመለከተ በሰጡን ማብራሪያ፤ ፓርኩ ለሚዝናኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹ፣ ደረጃውን ጠብቆ እና መሟላት ያለባቸው ነገሮች ተሟልተውለት ታድሷል። በዚህም በፓርኩ ለህፃናት የሚሆኑ መጫወቻዎች፣ የደከመ አካልንና አዕምሮን ጭምር ማሳረፊያ ወንበሮች፣ ዓይንን የሚስብ ፋውንቴን፣ የማታ ፍካት የሆኑ መብራቶች፣ መፀዳጃ ቤት፣ ምግብ ቤት፣ የጀበናና የማሽን ቡና የያዘ የካፍቴሪያ አገልግሎት እንዲሁም ስልክንም ይሁን ላፕቶፕን ቻርጅ ማድረጊያ ሶኬቶች የተሟሉለት ነው፡፡    

እንደ ማናጀሯ ገለጻ፣ ፓርኩ ህፃናት የሚጫወቱበት፣ መፃሕፍት የሚያነቡበት፣ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚደረጉበት፣ ወላጆች የልጆቻቸውን ልደት የሚያከብሩበት፣ ሙሽሮች የፎቶ መርሃ ግብር የሚያካሂዱበትና የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር የሚዝናኑበት ነው፡፡    

በፓርኩ ማህበረሰቡ ንፁህ አየር መቀበል የሚችልበት፣ ሊዝናና የመጣ ሰው ያለገደብ መዝናናት የሚችልበት፣ ከመደበኛ ምግብ ውጭ ማታ ላይ ለሚመጡ ችፕስ፣ ፒዛና በርገር የሚያገኙበት፣  ጥሩ ጊዜ የሚያሳልፉበት መሆኑን የነገሩን ማናጀሯ፤ “ለዚህም የሚመጡ ደንበኞች ምስክር ናቸው። በስራ ቀን ከ60 እስከ 70 እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ቁጥራቸው ባይታወቅም በርከት ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በፓርኩ ይዝናናሉ፡፡ ከክፍያ ውጭ ምሳ ለመመገብ የሚገቡ ሰራተኞችም ብዙ ናቸው” ሲሉ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ገልፀውልናል፡፡ ነዋሪዎች የመንፈስ ደስታ፣ የስሜት እርካታ አግኝተው እንዲመለሱ ከልጆች መጫወቻ ጋር ተያይዞ ኬክ እና አይስክሬም እንዲሁም ስጋ ቤት ለመክፈት የወደፊት እቅድ እንዳላቸውም አክለዋል፡፡  

በአዲስ አበባ ከተማ እድሳት የተደረገላቸው የህዝብ መናፈሻና መዝናኛ ፓርኮች እየሰጡት ያለውን አገልግሎት አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን የምህንድስና ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ገረመው ወርቁ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በአዲስ አበባ ነባርና ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ብዙ ፓርኮች ለምተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ እነዚህ ፓርኮች ማህበረሰቡ እንዲጠቀምባቸው ምቹ እየተደረጉ ነው፡፡ 

እነዚህ እድሳት የተደረገላቸው ፓርኮች የከተማዋን አጠቃላይ ገፅታ የሚቀይሩ፣ በኢኮኖሚውም የራሳቸው ጉልህ ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡ እንጦጦ ፓርክ፣ ፒኮክ መናፈሻ፣ አምባሳደር ፓርክ፣ የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ፣ ሃምሌ 19 ፓርኮች እድሳት የተደረገላቸው መሆኑን የገለፁት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ እነዚህም በሚጠበቀው አግባብ ወይም ዘመኑ በደረሰበትና ትውልዱ በሚፈልገው አንፃር የታደሱና እየታደሱ ያሉ ናቸው፡፡ 

እድሳቱ ተጠናቅቆ ወደ ስራ የገባው በመሃል ከተማ የሚገኘው አምባሳደር ፓርክ ከመታደሱ በፊት በፅዳቱ፣ ውስጥ ላይ በነበሩ መሰረተ ልማቶች በጣም የተጎዳና ለማህበረሰቡም ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየ ነበር፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ እድሳት የተደረገለት ፓርኩ፤ የመናፈሻ፣ የካፍቴሪያ፣ የልጆች መጫወቻ ተሟልተውለት፣ ምቹ፣ ደረጃውን በጠበቀ እና ትውልዱንም  በሚመጥን መንገድ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀውልናል፡፡  

መዲናዋ ለኑሮም ይሁን ለመዝናናት ምቹ ያልሆነች፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራ ያልነበሯት  ነበረች፡፡ ይህንን ታሳቢ ያደረገ 104 ከኮሪደር ልማቱ ጋር የለሙና 22 ነባር  ፓርኮች  እንዳሉ የሚናገሩት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ እነዚህ ፓርኮች የልጆች መጫወቻዎች ያሏቸው፣ የማህበረሰቡን አቅም ያገናዘቡ፣ ነዋሪዎች ራሳቸውን ከተፈጥሮ ጋር የሚያስተዋውቁባቸው፣ ንፁህ አየር የሚያገኙባቸው፣ ጭንቀታቸውን በማስወገድ ጤናቸውን የሚጠብቁባቸው፣ ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ እንዳያውሉ የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ የሚሰጡትን ዘርፈ ብዙ ጥቅም አብራርተዋል፡፡    

ፓርኮቹ  በዘመናዊ መንገድ የለሙና ከተማዋን ውበት ያላበሱ፣ ምጣኔ ሃብቷንም የጨመሩ፣ አዲስ አበባ እውነትም የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ የዲፕሎማቶች መቀመጫ መሆኗን ያረጋገጡ፣ ለነዋሪውም የመዝናናትን እድል የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም፤ በከተማዋ ያሉ ፓርኮች በዋጋ የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ያገናዘቡ፣ አንዳንዶቹም በነፃ ያለማንም ከልካይ እንዲዝናኑ የሚጋብዙ እንደሆኑ ገልፀው፤ እነዚህን መንግስት ብዙ ወጭ ያወጣባቸውን መዝናኛ ቦታዎች ማህበረሰቡ እንደራሱ ንብረት የመንከባከብ፣ የመጠበቅ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ እንዲውሉና በእጃቸው ያለውን ንብረት እንዲያውቁ የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review