በኮንስትራክሽን ግብአት አከፋፋይ ነጋዴዎች ላይ በተካሄደ የታክስ ኦፕሬሽን ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing በኮንስትራክሽን ግብአት አከፋፋይ ነጋዴዎች ላይ በተካሄደ የታክስ ኦፕሬሽን ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN- ጥር 9 / 2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የግብር ስወራን ለመከላከልና የንግድ ሥርዓቱን ፍትሀዊነት ለማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተከናወነ የተጠና፣ የተቀናጀና ድንገተኛ ኦፕሬሽን ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ 11 የኮንስትራክሽ ግብአቶችን በማከፋፈል ንግድ ላይ የተሰማሩ ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳውቋል።

ቢሮው አርብ ጥር 8 ቀን 2018 ዓ.ም መርካቶን ጨምሮ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የኮንስትራክሽን ግብአቶች በሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች ላይ ባካሄደው የተጠና የኦፕሬሽን ተግባር 10 ድርጅቶች በሕግ የተጣለባቸውን የደረሰኝ አጠቃቀም ግዴታ ባለመወጣት ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል።

በዚህም ከድርጊቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው 11 የንግድ ስራው ባለቤቶችና ሽያጩን ያለደረሰኝ ሲያከናውኑ የነበሩ ሰራተኞች የመንግስትን ግብር ለመሰወር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተገኝተው በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን አሳውቋል፡፡

የኦፕሬሽን ተግባሩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ማካሄዱን የገለጸው ቢሮው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የመንግሰትን ጥቅም ለማሳጣት ከታክስ አስተዳደር አዋጅ በተፃረረ መልኩ ያለደረሰኝ ሽያጭ በመፈፀም ወንጀል ተጠርጥረው በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው በፖሊስ ተይዞ ለፍርድ የሚቀርቡ ይሆናል ብሏል፡፡

በቀጣይ ቀናትም ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩን በሌሎችም ዘርፎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ቢሮው ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጎማና በኤሌክትሮኒክስ ነጋዴዎች ላይ ባካሄደው ተመሳሳይ ድንገተኛ የኦፕሬሽን ተግባር 20 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review