የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “አብሮነት ፣ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለጥምቀት ድምቀት” በሚል መሪ ሀሳብ የከተራና የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ጃንሜዳ የጽዳት ዘመቻ አካሄደ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ እንደተናገሩት፣ የጥምቀት በዓል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን በዓል ነው ሁላችንም ለበዓሉ ድምቀት የጋራ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በልዩ ሁኔታ ያደምቀዋል ሲሉም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ፣ በዓለ ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን ያስተማረበት በዓል ነው ብለዋል።
ከኢየሱስ ክርስቶስ እኛም የምንማረው ለሀገር እና ለህዝብ ትሁት እንሁን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የበዓሉን ድባብ የሚያደበዝዝ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ በጋራ መከላከል እንደሚገባም አንስተዋል።
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ፣ ዛሬ እዚህ የተገኘውን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ያለንን ክብር ለመግለጽ፣ በዓሉ የአብሮነት እና የወንድማማችነት መገለጫ በመሆኑ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ፀሐፊ ሼህ አብዱልሃሚድ አህመድ የጥምቀት በዓል የእኛ የሙስሊሞች በዓልም ነው፣ ለበዓሉ ድምቀት በጋራ እንቆማለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን አንድነት ህብረት ለማጽናት አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆም አለብን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጽዳት ዘመቻው ከተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ ወጣቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
የከተራ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓላት የፊታችን ጥር 10፣ 11 እና 12 በተከታታይነት በድምቀት ይከበራሉ፡፡
በዳንኤል መላኩ