የኢትዮጵያ ዕድገትና ህልም ሊሳካ የሚችለው በጠንካራ ተቋማት ግንባታ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢትዮጵያ ዕድገትና ህልም ሊሳካ የሚችለው በጠንካራ ተቋማት ግንባታ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)

AMN- ጥር 9/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ዕድገትና ህልም ሊሳካ የሚችለው በጠንካራ ተቋማት ግንባታ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ” ኮንፈረንስ ላይ ውይይት አድርገዋል።

በውይይት መርሐ-ግብሩም በሀሳብ፣ በግለሰብ እና ተቋም ላይ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን ተቋማዊ ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት ጥቂት ዓመታት ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም በዋናነት ተቋማትን በማዘመንና አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ላይ ያተኮረ መሆኑም ገልፀዋል።

ሪፎርሙ የሀገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን “ትሪፕል አይ” (III) የተሰኘ የተቀናጀ ስትራቴጂ እየተከተለ መሆኑን አብራርተዋል።

ተቋማዊ ግንባታና የለውጡ ፍልስፍና የተቋማት ሪፎርም መነሻው ፍላጎት መሆኑን የሚጠቁመው ይኸው መረጃ፣ ማንኛውም ትልቅ ህልም ሊሳካ የሚችለው በጠንካራ ተቋማት ብቻ መሆኑን ያብራራልም ብለዋል።

በዚህም መሰረት ሀሳብ የሁሉ ነገር ስርና መሰረት፣ ግለሰብ ሀሳቡን ተረድቶ የሚሸከም አመራር እንዲሁም ተቋም ሀሳብን ወደ ተግባር ቀይሮ ዘመን ተሻጋሪ የሚያደርግ መዋቅር፣ ተያይዘው ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት አንዷ ብትሆንም፣ እንደ ካፒታል ገበያ እና ሶቨሪን ዌልዝ ፈንድ ያሉ ወሳኝ ተቋማት ሳይኖሯት መቆየቷ የሪፎርሙን አስፈላጊነት የሚያጎሉ ማሳያዎችም መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢኮኖሚው ዋነኛ ስብራት የሚታይባቸው የዋጋ ንረት፣ የስራ አጥነት እና የንግድ ሚዛን ችግሮች በተናጠል ሊፈቱ እንደማይችሉ ተጠቁሟል።

እነዚህን ጉዳዮች ለማስታረቅ የፋይናንስ ሴክተሩን ፈትሾ መግራት እንደሚገባም ገልፀዋል።

በተለይም የባንክ አገልግሎትን ጥራት ማሻሻልና በቴክኖሎጂ መደገፍ ለኢኮኖሚው ቅልጥፍና ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ማኒስትሩ፣ ቀደም ሲል ለትንሽ የገንዘብ ዝውውር ይባክን የነበረውን ጊዜና ወጪ በአሁኑ ወቅት በዲጂታል አማራጮች ማቅለል መቻሉ እንደ ትልቅ የተቋማዊ ሪፎርም ውጤት ነው ብለዋል።

ሪፎርሙ አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግ፣ የህግ አስከባሪ ተቋማትን በማዘመን እና እንደ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ሳይበር ሴኩሪቲ ያሉ ዘመናዊ መዋቅሮችን በመገንባት 130 ሚሊየን ህዝብን መሸከም የሚችል የኢኮኖሚ አውድ ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሀሳብ በተቋምና በግለሰብ ላይ የሚደረገው ሪፎርም የኢትዮጵያ ዕድገትና ህልም ለማሳካት ቁልፍ ሚና የሚጫወት በመሆኑ፣ ጠንካራ የተቋማት ግንባታ አስፈላጊ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review