በአይሾው ስፒድ ጉብኝት ምክንያት የቻይና ጎብኝዎች ቁጥር በ173% ጨምሯል

You are currently viewing በአይሾው ስፒድ ጉብኝት ምክንያት የቻይና ጎብኝዎች ቁጥር በ173% ጨምሯል

AMN – ጥር 9/2018 ዓ.ም

ብዙዎች ቻይናን “ዝግ ሀገር” አድርገው ቢያስቡም፣ ታዋቂው ዩቲዩበር ዳረን ዋትኪንስ ጁኒየር (አይሾው ስፒድ) እ.ኤ.አ. በ2025 መጀመሪያ ላይ በቤጂንግ እና በሻንጋይ ጎዳናዎች ላይ በነጻነት ተመላልሶ በቀጥታ ስርጭት የሕዝቡን አኗኗር በማሳዬቱ የዓለምን ዓይን ወደ ምስራቋ ሀገር መልሷል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን ልብ የሰረቀው ይህ ጉብኝት ለቻይና የቱሪዝም መነቃቃት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፤ ምክንያቱም በቻይና ያደረገው ጉብኝት ከመዝናኛነት አልፎ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ መነቃቃት መፍጠር ችሏል።

ስፒድ እንደ ቤጂንግ፣ ሻንጋይ፣ ቾንግቺንግ እና ቼንግዱ ያሉ ከተሞችን ሲጎበኝ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቀጥታ ስርጭት መከታተላቸው የቻይና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አግዟል።

በቆየባቸው ቀናት በድምሩ ከ907 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቻይናን የተመነለከቱ ሲሆን በዚህ ጉዞው ምክንያት በ2025 የቻይና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር Trip.com እንደገለጸው ሰዎች ወደ ቻይና የሚያደርጉት የጉዞ ትዕዛዞች በ173% ጭማሪ አሳይቷል።

ስፒድ በሸንዘን (Shenzhen) ቆይታው በውሃ ላይ የሚንሳፈፈውን BYD Yangwang U8 መኪና በመንዳት እና ባለ ሶስት ተካፋዩን (Tri-fold) Huawei Mate XT ስልክ በቪዲዮው ላይ በማሳየት ትልቅ መነጋገሪያ ፈጥሯል።

የሀገሪቱን ገጽታ ከመገንባትም (Soft Power) አንጻር ብዙ ጊዜ በምዕራባውያን ሚዲያዎች ዘንድ “ዝግ እና ቁጥጥር የሚበዛባት” ተደርጋ ስለምትሳለው ቻይና ያለውን የተሳሳተ አመለካከት በተግባር ሰብሮታል።

ስፒድ ግን ያለምንም ገደብ በከተሞች ሲዘዋወር፣ ከሰዎች ጋር ሲጫወት እና በነፃነት ሲንቀሳቀስ ማሳየቱ ዓለም ስለ ቻይና ያለውን አመለካከት እንዲቀይር አስገድዷል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይቀር ይህንን ጉዞ “የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ” በማለት ገልጾታል።

የስፒድ የሻኦሊን ኩንግ-ፉ ልምምዱ፣ የቻይና ኦፔራ ዕይታው እና እንደ ሮንግቻንግ ዳክዬ ያሉ የሀገር በቀል ምግቦችን መመገቡ የቻይናን ባሕል ለቢሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች አስተዋውቋል። ከጉዞው ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ይዘቶች በሁሉም የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በድምሩ 8.22 ቢሊዮን ጊዜ ታይተዋል።

የቻይናን የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ዕድገት እንደዋዛ ያሳየው ስፒድ በቻይና የፈጣን ባቡሮች (Bullet Trains) ውስጥ እንኳን ሳይቋረጥ የቀጥታ ስርጭት ማድረጉ የሀገሪቱን የ5G ቴክኖሎጂ ጥንካሬ ለዓለም አስመስክሯል። በቪዲዮዎቹ ላይ የታየው የከተሞች ንጽህና እና የሰላም ሁኔታ ቻይና ለቱሪስቶች አስተማማኝ መሆኗን አረጋግጧል።

እንደ CCTV ያሉ የቻይና መንግስታዊ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ለስፒድ ጉብኝት የ8 ደቂቃ ልዩ ሽፋን ሰጥተዋል። ይህም ቻይና ለዓለም አቀፍ ዝነኞች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ክፍት መሆኗን ለማሳየት የተጠቀሙበት ስትራቴጂ ነው።

በአጠቃላይ አይሾው ስፒድ በቻይና ቆይታው በዌይቦ (Weibo) በ3 ቀናት ውስጥ 2 ሚሊዮን ተከታዮችን በማግኘት እና በዩቲዩብ 38 ሚሊዮን ሰብስክራይበር በመድረስ የግል ክብረ ወሰኑን ሲያሻሽል፣ ለቻይና ደግሞ በገንዘብ የማይተመን ውለታ ውሎላታል።

በዚህ የተነሳ አይሾው ስፒድ ለቻይና እንደ አምባሳደር ሆኖ አገልግሏል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ቻይናን እንደ ዘመናዊ፣ አስደሳች እና ተስማሚ የጉዞ መዳረሻ አድርገው እንዲያዩ በማድረግ ረገድ ትልቁን ድርሻ ወስዷል።

በአጠቃላይ የቻይና መንግስት ይዞታ የሆኑት እንደ CCTV እና Global Times ያሉ ሚዲያዎች፣ የስፒድን ጉብኝት ተከትሎ በሀገሪቱ የቱሪዝም ፍላጎት ላይ የታየውን ለውጥ “The Speed Effect” በሚሉ ርዕሶች ዘግበውታል። የእሱ መምጣት በወጣቱ ትውልድ ዘንድ ቻይናን ዳግም “ተፈላጊ” እንድትሆን ማድረጉን ገልጸዋል።

የወጣቱ ዩትዩበር ጉብኝት ለኢትዮጵያስ ምን ዕድል ይዞላት ይመጣል ብላችሁ ታስባላችሁ?

ፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review