የማንችስተር ዩናይትድ የምንጊዜም ታላቁ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በዙፋናቸው በነበሩበት ወቅት ከማንችስተር ሲቲ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ አያስጨንቃቸውም ነበር።
በዓመታት ውስጥ ብልጭ ከሚል ድል ውጪ የፈተናቸው ቡድን ባለመሆኑ “ጩኸታሞቹ ጎረቤቶች” እስከማለት ደርሰዋል። ሰር አሌክስ በወቅቱ ምንም ቢሉ እሳቸውን መከራከር ከባድ ነው። ምክንያቱም ጩኸት ብቻ ያሉትን ቡድን ደግመው ደጋግመው ድል አድርገውታል።
አሁን ያሁሉ ተረት ሆኗል። በክብር ያስረከቡት ዙፋን ተረጋግቶ የሚቀመጥበት አሰልጣኝ አጥቷል። ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተዋቀረ በኋላ ክለቡ በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ዝቅታ ላይ ይገኛል። በተለያየ መንግድ ስኬት አስመዝግበው የመጡ አሰልጣኞች በዩናይትድ ክብር እና ዝናቸው ተገፏል።
ስራቸው ከሰር አሌክስ የገዘፈ ታሪክ ጋር እየተነፃፀረ ብዙም ሳይጓዙ ተደናቅፈዋል። አዙሪቱ አሁንም አለቀቃቸውም ፤ 10 ሚሊየን ፓውንድ ማካካሻ ከፍለው የሾሙት ሩበን አሞሪምን አሰናብተዋል።
የቀድሞ ተጫዋቻቸው ዳረን ፍሌቸር ሁለት ጨዋታዎችን እንዲመራ ፈቅደው ከ3ኛ ዙር የኤፍ ኤካፕ ውድድር ውጪ ሆነዋል። ክለቡ በ3ኛው ዙር የኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ሲወጣ ከ12 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ከካራባኦ ካፕ ውድድር ቀድሞ የወጣው ዩናይትድ በውድድር ዓመቱ 40 ጨዋታ ብቻ ያከናውናል። ይህም ከ111 ዓመታት በኋላ ትንሽ ጨዋታ የሚያደርግበት ዓመት ይሆናል።
ዩናይትድ አሁን ላይ የውድድር ዓመቱን እንዲያድንለት ሌላ የቀድሞ ባለታሪኩ ማይክል ካሪክን ሾሟል።
በውሃ ሰማያዊዎቹ ቤት ግን ታሪኩ ሌላ ነው። በስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ “ጩኸታም ጎረቤቶች” የተሰኙት ማንችስተር ሲቲዎች ከከተማው አልፈው ከአውሮፓ ምርጥ ክለቦች አንዱ ሆነዋል። ሰር አሌክስ እያሉም የጀመረው ስኬታቸው ፔፕ ጋርዲዮላ ወደ ሌላ ከፍታ ሰቅሎታል።
ስፔናዊ አሰልጣኝ ገናናው ዩናይትድ እንኳን ያላሳካቸውን ታሪኮች አስመዝግቧል። በውድድር ዓመት 100 ነጥብ ያመጣ ቡድን ገንብቷል ፣ አራት ተከታታይ የውድድር ዓመት የሊጉ ቁንጮ የሆነ ቡድን አሳይቷል። ቀዮቹ የሚኩራሩበት የሦስትዮሽ ድልንም ተጋርቷል።
አሁን ተራው የማንችስተር ሲቲ ደጋፊዎች ከዩናይትድ ጋር ሲጫወቱ ብዙም ከቁብ የማይቆጥሩት ጨዋታ ሆኗል። የእነርሱ ትኩረት አርሰናል እና ሊቨርፑል ላይ ነው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሆኑት ሁለቱ ክለቦች ዛሬ 198ኛ የደርቢ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። በኦልድትራፎርድ በሚደረገው ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ሦስት ነጥቡ ያስፈልጋቸዋል።
ሲቲ ከመሪው አርሰናል ላለመራቅ ፣ ዩናይትድ ደግሞ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ የሚያደርገው ደረጃን ለመያዝ ድሉ ያስፈልጋቸዋል። ኦሌገነር ሶልሻየር ሲሰናበት ማንችስተር ዩናይትድን በሦስት ጨዋታዎች በጊዜያዊነት የመራው ማይክል ካሪክ አሁን በምን መልኩ ቡድኑን እንደሚያዋቅር ለማየት ያጓጓል።
እንግሊዛዊው አሰልጣኝ ከአፍሪካ ዋንጫው የተመለሱት ብሪያን ምቡሞ እና አማድ ዲያሎን በስብስቡ ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል። ማይክል ካሪክ ከተከላካዩ ማቲያስ ደሊግት ውጪ የተሟላ ስብስብ አለው።
የተከላካይ ክፍሉ በጉዳት የሳሳበት ማንችስተር ሲቲ ይበልጥ በአጥቂዎቹ ይተማመናል። ማርክ ገሂን ለማስፈረም የተስማማው ሲቲ አዲስ ፈራሚው አንቷን ሴሜንዮ በፍጥነት ተላምዶለታል።
ሲቲ በኦልድትራፎርድ ያለው ክብረወሰንም የሚያኩራራ ነው። በተቀናቃኙ ሜዳ ዘጠኝ ጣፋጭ ድሎችን አግኝቷል። ይህም ከየትኛውም ክለብ የበለጠ በኦልድትራፎርድ በርካት ድል ያገኘ ክለብ እንዲባል አስችሎታል።
የዛሬው ጨዋታ ቀን 9:30 ይከናወናል። የማንችስተር ከተማ ተወላጁ አንቶኒ ቴይለር በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሸዋንግዛው ግርማ