ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በ6 ዓመት ለመሰብሰብ ያዳግታት የነበረውን የገቢ መጠን በያዝነው ዓመት በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ማሳካት መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
“የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የፋይናንስ ኮንፈረንስ ላይ ኢትዮጵያ በታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓት ላይ ያደረገችው ማሻሻያ ስላመጣው ውጤት ገለጻ አድርገዋል።
የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሁም ግብር የሚሰበሰቡባቸውን አማራጮች ማስፋት በመቻሉ፣ ባለፉት 6 ወራት 709 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል። ከለውጡ በፊት በነበሩት 6 ዓመታት የተገኘው ገቢ በድምሩ 595 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያነጻጸሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድሮ በ6 ወራት የተገኘው ገቢ ብቻ የ115 ቢሊዮን ብር ብልጫ አምጥቷል።
በተያዘው ዓመት መንግስት ከሀገሪቱ ለመሰብሰብ ካቀደው 2.5 ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ ግብር እና ታክስ ውስጥ 1 ትሪሊዮን ብር የሚሆነውን ክልሎች እንዲያመነጩ ዕቅድ ተይዟል፤ ቀሪው 1.5 ትሪሊዮን ብር ደግሞ ከፌደራል መንግስት ለመሰብሰብ የታሰበ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደገለጹት ለዚህ ሁሉ ስኬት ትልቁ ሚስጥር መንግስት የያዘው ሀገር በቀል የሆነ የተቋማት ማሻሻያ ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት በመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።