ከታሪካዊቷ ጎንደር እስከ መላው ኢትዮጵያ የሚያቀናው አዲሱ የባህል ጥበባት የሚዲያ ፎረም

You are currently viewing ከታሪካዊቷ ጎንደር እስከ መላው ኢትዮጵያ የሚያቀናው አዲሱ የባህል ጥበባት የሚዲያ ፎረም

AMN ጥር 09/2018 ዓ.ም

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሀገር ባህልንና እድገትን ማስተዋወቅ ያለመ አዲስ የባህል ጥበባት ሚዲያ ፎረም ማዘጋጀቱን አስታወቀ

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተቋቋመው የባህልና ጥበባት የሚዲያ ፎረም፣ የ”ሚዲያ ቱር” ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን በማስመልከት በጎንደር ከተማ ለሚዲያ አካላት መግለጫ ሰጥቷል።

ፎረሙን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሃይማኖት ዓለማየሁ፤ የኢትዮጵያን ባህል፣ ሀብትና አቅም ለማስተዋወቅ የሚዲያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጥር 7 ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያን አንድነት፣ አብሮነትና ትስስር ማጠናከርን ያለመ ዝግጅት በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ሲካሄድ መቆየቱን ያነሱት ወ/ሮ ሃይማኖት፤ ቀጣዩ የጥምቀትና የከተራ በዓላትም ባህላዊና ትውፊታዊ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

በባህልና ስፖርት የሚዲያ ፎረም ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ በፈቃዱ አባይ በበኩሉ፤ በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ በይፋ የሚጀመረው የሚዲያ ቱር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የሀገሪቱን ባህል፣ ቅርስና ሀገር በቀል ዕውቀቶች እንደሚሰንድና እንደሚያሳውቅ ተናግሯል።

አዲሱ የባህል ጥበባት የሚዲያ ፎረም የኪነ ጥበብ ሰዎችንና ልምድ ያላቸውን የሚዲያ ባለሙያዎችን ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ያቀፈ ሲሆን፣ ሰፊ ዓላማና ግብ ያለው መሆኑም ተገልጿል።

ጋዜጠኛና የሚዲያ ፎረሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኤሊያስ ተክለወልድ በበኩሉ፤ የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግና ቅርስ እንዲሁም አጠቃላይ አቅም ለማስተዋወቅ እንዲህ ዓይነት የሚዲያና የባህል ፎረም መዘጋጀቱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሷል። ኤሊያስ አክሎም፤ የሕዝብን አብሮነት፣ እድገትና እሴቶችን ይበልጥ ለማሳወቅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን መሰል ፎረም ማዘጋጀቱ የሚደነቅ መሆኑን ገልጿል።

በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፣ የቀጣይ ተግባራት አቅጣጫም ተቀምጧል።

በአፈወርቅ ውበቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review