የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያና በሌሎች የዓለም ሀገራት

You are currently viewing የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያና በሌሎች የዓለም ሀገራት

AMN – ጥር 8/2018 ዓ.ም

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ዘንድ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩና በርካታ ሕዝብን ከሚያሳትፉ የ”አደባባይ በዓላት” መካከል ቀዳሚው ነው።

በዓሉ በሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ (UNESCO) በማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ መመዝገቡ ይታወቃል።

የበዓሉ አከባበር በኢትዮጵያና በሌሎች የዓለም ሀገራት እንደየሀገራቱ ባህልና እንደ አብያተ ክርስቲያናቱ ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል፡፡

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶችን አጣምሮ የያዘ ነው።

አከባበሩ የሚጀምረው ከጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ጀምሮ ሲሆን፣ ዕለቱም “ከተራ” በመባል ይታወቃል።

በዚህ ዕለት ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው ወደ “ጥምቀተ ባሕር” በታላቅ ዝማሬና በምእመናን አጀብ ይጓዛሉ፤ በዚያም በጸሎት ያድራሉ፡፡

በማግስቱ ጥር 11 ቀን ማለዳ ላይ የጥምቀት በዓሉ ይከናወናል። ካህናቱ የባሕሩን ውሃ ይባርካሉ፤ ከዚያም በዮርዳኖስ ወንዝ የተከናወነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት ለማስታወስ የተባረከውን ውሃ በምእመናን ላይ ይረጫሉ።

በዓሉ በተለይም ደግሞ ታዳጊ ወጣቶች አዲስ ልብስ የሚለብሱበት፣ ወጣቶች የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት፣ ሎሚ ውርወራ እና ልዩ ልዩ ባህላዊ ጨዋታዎች የሚከናወኑበት ነው።

ጥር 11 ቀን ታቦታቱ ካደሩበት ባሕረ ጥምቀት በታላቅ ዝማሬና በምእመናን አጀብ ወደየአድባራቶቻቸው ይመለሳሉ።

በዕለቱ ወደ መንበረ ክብራቸው ያልተመለሱ ታቦታት ደግሞ በማግስቱ ጥር 12 ቀን በታላቅ ሥነ-ሥርዓት ይመለሳሉ፤ ይህም ዕለት ቃና ዘገሊላ ተብሎ በልዩ ሁኔታ ይከበራል፡፡

የጥምቀት በዓል በሌሎች የዓለም ሀገራት
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ “ኤፒፋኒ” (Epiphany) ተብሎ የሚጠራው ይህ በዓል፣ በሌሎች ሀገራትም እንደየ ባህላቸው በተለያዩ መንገዶች ይከበራል።

በምስራቅ አውሮፓ (ግሪክ፣ ሩሲያና ቡልጋሪያ)፦ በእነዚህ ሀገራት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ-ክርስቲያን በዓሉን የምታከብረው ከውኃ ጋር በተያያዘ ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡

በግሪክና በቡልጋሪያ ካህኑ መስቀልን ወደ ቀዝቃዛ ባሕር ወይም ወንዝ ውስጥ ይወረውራሉ። ወጣቶችም መስቀሉን ለማውጣት ወደ በረዶው ውሃ ውስጥ ዘለው ይገባሉ። መስቀሉን ቀድሞ ያገኘ ሰው በዚያ ዓመት የተባረከ እንደሚሆን ይታመናል።

በሩሲያም ምእመናን በመስቀል ቅርፅ በተሠራና ቅዝቃዜው በበረታ የበረዶ ውሃ ውስጥ በመግባት ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን ይፈጽማሉ።

በምዕራብ አውሮፓና ላቲን አሜሪካ (ስፔንና ሜክሲኮ)፦ በነዚህ ሀገራት በዓሉ ይበልጥ የሚያተኩረው ሰብአ ሰገል ሕጻኑን ኢየሱስን ለመጎብኘት መምጣታቸውን በማስታወስ ነው፡፡

“ሰብአ ሰገል”ን የሚወክሉ ሰዎች በፈረስ ወይም በግመል ላይ ሆነው ለሕጻናት ከረሜላና ሌሎች ስጦታዎችን እያከፋፈሉ ሰልፍ ያደርጋሉ። በተጨማሪም “የነገስታት ኬክ” የተባለ የኬክ ዓይነት ይዘጋጃል፤ በኬኩ ውስጥ የሚደበቀውን የሕጻን ምስል ያገኘ ሰው ልዩ በዓል የማዘጋጀት ግዴታ ይኖርበታል።

በግብፅ፦ የጥምቀት በዓል “ጋታስ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ አከባበሩም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ምእመናን በናይል ወንዝ አካባቢ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚያከናውኑ ሲሆን፣ በባህላዊ መልኩ ደግሞ የሸንኮራ አገዳና ብርቱካን ለበዓሉ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል ታቦታቱ ከቤተ-ክርስቲያን ወጥተው በአደባባይ በታላቅ ሕዝባዊ አጀብ መከበሩ ከሌሎች ሀገራት ለየት ያደርገዋል።

በሌሎች ሀገራት ግን በዓሉ በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በሚደረግ ጸሎት አልያም በባሕር ውስጥ በሚከናወን “መስቀል የመፈለግ” ውድድር ይከበራል። መረጃውን ከተያየዩ ፅሑፎች ዋቢ አደረግን።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review