የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካለበት ወደ ላቀ ደረጃ በመሸጋገር እንዲሸጋገር መፍጠር፣ መፍጠን እና መዝለል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
“የፋይናንስ እምርታ በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የፋይናንስ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በፊንቴክ ቴክኖሎጂ ያለችበትን ደረጃ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከበርካታ የበለጸጉ ሀገራት ወደኋላ መቅረቷ አግባብነት እንደሌለዉ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን የርቀት ልዩነት ለማጥበብ የተለመደውን የዕድገት ፈለግ መከተል ብቻ በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
“ሌሎች ሀገራት በሄዱበት መንገድ እግር በእግር እየተከታተልን የምንሄድ ከሆነ፣ አንደኛ አንደርስባቸውም፤ ሁለተኛ ደግሞ አዳዲስ የርቀት ልዩነቶች ይፈጠራሉ” ብለዋል።
ስለሆነም የኢትዮጵያን ችግር ቀርፎ ከሌሎች ጋር እኩል ለመቆም የእድገት ደረጃዎችን መዝለል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በሃገሪቱ ለአዳዲስ እውቀትና ለውጦች የመለማመድ ፍላጎታቸው አነስተኛ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በማናውቀውና ባልሰራንበት ዘርፍ ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች አዳዲስ ሀሳቦች እንዳይፈጠሩ እንቅፋት እንደሚሆኑ በምሳሌነት አስረድተዋል።

አሁን ላይ ያሉ ትናንሽ ጅማሮዎች የሚበረታቱ ቢሆኑም፣ ወደታለመው ደረጃ ለመድረስ ግን አሁንም መፍጠር፣ መፍጠን እና መዝለል አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም በአሥረኛ ደረጃ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላትና አብዛኛው ዜጋዋ ወጣት መሆኑ ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ይህ ወጣት ትውልድ፦
ትልቅ ራዕይ እንዲኖረው ነገን ለማየት እንዲመኝና እንዲጓጓ፣የሥራ ባሕልን እንዲላበስ ከተደረገ፣ ኢትዮጵያ የሚገባት ደረጃ ላይ እንደምትደርስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ወቅታዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከጥልቅ እንቅልፍ ነቅቶ እንደሚንጠራራ ሰው የመሰሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “የሚያኩራራ ቦታ ላይ ባንደርስም፣ ከእንቅልፋችን ነቅተን እየተንጠራራን ነው” ብለዋል።
ኢኮኖሚው መራመድ እንዲጀምርና ወደምንፈልገው ግብ እንዲደርስ የሁሉንም እገዛና ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ