የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ለተቋማዊ ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ለተቋማዊ ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN – ጥር 10/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ” በሚል በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ተቋማዊ ሪፎርም ላይ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፣ አሁን ያለውን የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ፍላጎትና አቅም ለመሸከም ነባር አሠራሮችን ማዘመን የግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።

ተቋማት ካልተገነቡ በስተቀር ሐሳብ ብቻውን ተሻግሮ ትልቅ ተፅዕኖ ሊያመጣ አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተቋም ግንባታ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት ዘመኑን የሚዋጅ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አገራት ተርታ ብትመደብም፣ እስከ ዛሬ ድረስ የካፒታል ገበያ ሳይኖራት መቆየቷ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሳይኖር ኢኮኖሚውን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት እንደማይቻልም ጠቁመዋል።

የፋይናንስ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ማሻሻያ እያደረገ ይገኛል። አዳዲስ የፋይናንስ አሠራሮችን የሚፈቅዱ ሕጎችን ማውጣትና የስትራቴጂ ለውጥ በማድረግ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ አቅጣጫዎች ተነድፈዋል።

የአመራርና የአሠራር ዘመናዊነትን ለማረጋገጥ ተቋማትን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የማደራጀት ሥራ በስፋት መከናወኑን ገልጸዋል።

ሀገሪቱ ወደፊት በምታደርገው የኢኮኖሚ ጉዞ ውስጥ የግሉ ዘርፍም ሆነ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸውን ዳግም በመዋቀር ለዘመናዊው የገበያ ሥርዓት ዝግጁ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review