ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከልዩነት ይልቅ አንድነታችንን በማስቀደም በሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ በመምከር የጥል እና የጥላቻ ግድግዳዎችን እናፍርስ ሲሉ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ ማለዳ በጃንሜዳ ተገኝተን ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት መታሰቢያ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለናል ብለዋል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከሀጥያት ሞት በፍቅር፣ በምህረቱና በርህራሄው ሊያድን ሰውን መስሎ ከድንግል ማሪያም በቤተልሔም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ለዓለም እንደተገለጠው ሁሉ፤ እኛም የጥምቀቱን ዓላማ ተረድተን በእለት እለት ህይወታችን ልንኖረው ይገባል።

ይህም ከቂምና ከጥላቻ ተላቀን፤ ከቂም ይልቅ ይቅርታን፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነታችንን በማስቀደም በሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ በመምከር የጥል እና የጥላቻ ግድግዳዎችን እናፍርስ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በምትኩም የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅርታ እና የአንድነት ድልድዮችን መገንባት ይጠበቅብናል።
የጥምቀት በዓል የእምነት መግለጫ ብቻ ሳይሆን፤ የአንድነታችን፣ የመፈቃቀራችን የሰላማችንና የኢትዮጵያዊ ጨዋነት መገለጫ የጋራ ውበታችን ነጸብራቅም ነው። መልካም በዓል በድጋሚ ሲሉ መልእክት አስተላልዋል፡፡