አዲስ አበባ እንደ ጥምቀቱ ምሳሌ አጊጣ፤ ጸድታ፣ ተዉባና ታድሳ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥታለች – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing አዲስ አበባ እንደ ጥምቀቱ ምሳሌ አጊጣ፤ ጸድታ፣ ተዉባና ታድሳ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥታለች – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ጥር 11/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ መዲናችን አዲስ አበባ እንደ ጥምቀቱ ምሳሌ አጊጣ፤ ጸድታ፣ ተዉባና ታድሳ ከበዓሉ ጋር አንድ ላይ አምራ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥታለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጃንሜዳ በተከበረዉ የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ በመገኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ጥምቀት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የዳግም ልደትና የመገለጥ ማሳያ ነዉ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓሉን ስናከብር የኢየሱስ ክርስቶስን ተምሳሌትነት በመከተል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር ከጥላቻና ከቂም በመራቅ፤ የክርክር እና የመራራቅ ግርግዳዎችን በማፍረስ ሊሆን ይገባል፡፡ በምትኩም የመዋደድ፤ የአንድነት፤ የአብሮነት፤ የመከባበር የሰላምና የፍቅር ድልድዮችን መገንባት ከሁሉም ይጠበቃል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡

ጥምቀት በዓለም በማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት ከተመዘገበ 6 አመታት ሆኖታል ያሉት ከንቲባዋ ይህ ዉብና ደማቅ ስርዓት ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ በተጨማሪ ባህላችንን፤ ቋንቋችንን እና ህብረብሔራዊ አንድነታችንን ለዓለም የምናሳይበት በዓል ነዉ ብለዋል፡፡

መዲናችን አዲስ አበባም እንደ ጥምቀቱ ምሳሌ አጊጣ፤ ጸድታ፣ ተዉባና ታድሳ ከበዓሉ ጋር አንድ ላይ ደምቃ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥታለች ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ ችላለች ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህንን ዉጤት ለማስመዝገብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋራ በጋራ ሰርተናል፤ ዉጤቱም የጋራችን ነዉ ብለዋል፡፡

በጃንሜዳ በተከበረዉ የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review