አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ” የ QS World University Rankings” በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚውን ደረጃ ይዟል።
ተቋሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየጊዜው በሚያስመዘግቧቸው የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ውጤቶች በየዓመቱ በመላው ዓለም ደረጃ ይወጣላቸዋል።
ይህ ደረጃ ተቋማቱ በሶስቱም ዘርፎች በሚያከናውኗቸው ተግባራት እና ተግባራቸው ከሀገራቸው አልፎ በሌሎችም ዘንድ የሚያመጣውን ተቀባይነት ከግምት በማስገባት የሚሰጥ ነው።
አፍሪካን ኢንሳይደር እንደዘገበው በዘንድሮው የ “QS World University Rankings” መሰረት ከምስራቅ አፍሪካ አራት ዩኒቨርሲቲዎች የቀጠናውን ተመራጭ ዩኒቨርሲቲነት ደረጃ ይዘዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በተከታታይ ባስመዘገቡት የማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ብቻም ሳይሆን በፈጠራ እና በቀጠናው ልማት ላይ ያበረከቱት አስተዋፅኦም ከግምት ውስጥ ገብቷል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ቀዳሚ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነውን እና ዘንድሮ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመቱን እያከበረ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀዳሚነት የተመረጠ ሲሆን የዩጋንዳው ማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ፣የኬንያው ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ እንዲሁም የሱዳኑ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካርቱም አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቀዳሚው እና ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ያስታወሰው ቢዝነስ ኢንሳይደር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱ የዕውቀት የጀርባ አጥንት ሆኖ በማገልገል ለ75 ዓመታት ለሀገሪቱ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ምሁራን፣ ባለሙያዎች እና የሀገር አስተዳዳሪዎችን እንዳፈራ በዘገባው ገልጿል።
በዘንድሮው ምርጫም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሂውማኒቲስ፣ ሶሻል ሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግ እና የጤና ሳይንስ ጠንካራ ስራዎችን የሰራ ሲሆን በርካታ የምርምር ተቋማቱም ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ሲል አመልክቷል።
በዚህም ስራው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሀገሩ ኢትዮጵያ ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ትልቅ ሚና የሚጫወት ቁልፍ ተቋም ነው ሲል ቢዝነስ ኢንሳይደርን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።