የጥምቀት በዓል አከባበርና ሃይማኖታዊ ስርዓት አስደናቂና ቀልብን የሚስብ ነው ሲሉ በጉራጌ ዞን እምድብር ተገኝተው በበዓሉ የታደሙ የውጭ ሀገር ዜጎች ገለጹ፡፡
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በታላቅ ድምቀት ከተከበረባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምድብር ሃገረ ስብከት ነው።
በዓሉን የታደሙ የውጭ ሀገር ዜጎች እንደገለጹት፥ የጥምቀት በዓል አከባበርና ሃይማኖታዊ ስርዓት ቀልብን የሚስብ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓትና ባህላዊ ክዋኔዎች ቀልብን የሚስብና ማራኪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ከጀርመን የፖደቦርን ሃገረስብከት ጳጳስ አቡነ ማትያስ የምዕመኑ ህብረ ዝማሬ መንፈስን የሚያድስ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውብ መንፈሳዊ የጥምቀት ስርአት ለመጀመሪያ ጊዜ መታደማቸውንና በህዝቡ እንግዳ ተቀባይነትም መደነቃቸውን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ አየር ተስማሚነት፣ በስነ ምድሩ ማራኪነትና አረንጓዴነትም መደመማቸውን ጠቁመው ወደፊት የሀገራቸው ዜጎች እንዲጎበኙ እንደሚጋብዟቸው አመላክተዋል።
ከካናዳ የመጡት ዶናልድ ካኖልድ በበኩላቸው፥ የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያውያን በሀገር ባህል ልብስ ተውበው በአብሮነት የሚያከብሩት ጥልቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓት መሆኑን ተመልክቻለሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያ መጥተው በበዓሉ በመታደማቸው ደስታ እንደተሰማቸው የገለጹት ደግሞ ሌላው ጎብኚ ዶሚንኬ ካሮን ናቸው፡፡
በበዓሉ መታደማቸው መንፈሳቸውን ማደሳቸውንና የማይረሳ ጊዜያት ማሳለፋቸውን አመልክተዋል።
ሌላዋ በበዓሉ የታደመችው ጣሊያናዊት ጎብኚና የማህበራዊ ሚድያ ባለሞያ ኢዝቤላ ፑችኒ ” ባየሁት ነገር ተገርሚያለሁ፤የበዓሉን አከባበር ለዓለም አስተዋውቃለሁ ” ብላለች።
በጥምቀት በዓል የሚከናወኑ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ክዋኔዎች እጅግ ማራኪና የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ እንደሆኑም ጎብኚዎቹ መግለፃቸውን የኢዜአ መረጃ ያመላክታል።