በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከበረው የጥምቀት በዓል አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በስኬት እና በደመቀ መልኩ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በመላው ሀገራችን በታላቅ ድምቀት የተከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር በመቀናጀት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሰፊ የሰው ኃይል በማሰማራት ተገቢውን የፀጥታ ሥራ በማከናወን ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል።

የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ መሠረት በማድረግ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት በማስቀደም ከከተራ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተጠናከረ ጥበቃ በማከናወን በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት አመራሮችና አባላት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል።

ለፀጥታና ደኅንነት አካላት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ ላበረከቱት ለሃይማኖት አባቶች፣ ለበዓሉ አስተባባሪዎች፣ ለእምነቱ ተከታዮች እና ለወጣቶች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረበ በነገው ዕለት የሚከበረው ቃና ዘገሊላ በዓልም በስኬት እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ለኤ.ኤም.ኤን በላከው መረጃ ጥሪ አቅርቧል።