የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎማለፍ ተወዳዳሪዎቹን ለመለየት ተቃርቧል። የሊግ ምዕራፍ ሰባተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይከናወናሉ። ዛሬ ከሚከናወኑ ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ኢንተር ሚላን ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ በትልቁ ይጠበቃል።
አርሰናል ስድስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ የሊግ ምዕራፍ የደረጃ ሰንጠረዥን እየመራ ይገኛል። የሰሜን ለንደኑ ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ባየርን ሙኒክ የመሳሰሉ የአውሮፓ ጠንካራ ክለቦችን ገጥሞ አሸንፏል። ከስድስት ጨዋታም የተቆጠረበት አንድ ግብ ብቻ ነው።
በሊጉ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ የተከታዮቹን ነጥብ መጣል ያልተጠቀመበት አርሰናል በዛሬው ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘት ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር ያሳልፈዋል።
በሊግ ምዕራፍ ከ1-8 ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ 16 ቡድኖች ወደ ሚፋለሙበት ጥሎ ማለፍ ቀጥታ ያልፋሉ። ከ9-24 የሚያጠናቅቁ ደግሞ እርስ በእርስ ተጫውተው አሸናፊ ስምንት ክለቦች ጥሎ ማለፉን ይቀላቀላሉ።
አርሰናል ተሸንፎም ቀጥታ ማለፉን የሚያረጋግጥበት ምሽት ይሆናል። የፊታችን እሁድ በፕሪሚየር ሊጉ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ፈታኝ ጨዋታ ያለበት አርሰናል ለተወሰኑ ተጫዋቾቹ እረፍት ሊሰጥ ይችላል።

የሴሪ አው መሪ ኢንተር ሚላን ሦስት ነጥቡ ከተጋጣሚው የበለጠ ያስፈልገዋል። የጣልያኑ ክለብ 12 ነጥብ በመሠሰብሰብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች ባለፈው የውድድር ዓመት በተመሳሳይ በሊግ ምዕራፍ ላይ ተገናኝተው ኢንተር በሃካን ቻልሃኖግሉ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል።
ከዚህ ውጪ የሁለቱ ክለቦች ግንኙነት ከ23 ዓመታት በፊት በምድብ በደርሶመልስ ያደረጉት ጨዋታዎች ነው። አርሰናል በቀድሞው ስታዲየሙ ሃይበሪ 3ለ0 ሲሸነፍ በጁሴፔ ሜይዛ ስታዲየም በቴሪ ኦንሪ ሃትሪክ ታግዞ 5ለ1 መርታቱ ይታወሳል።
የዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 5 ሰዓት በጁሴፔ ሜይዛ ስታዲየም ይከናወናል። ጨዋታውን ፖርቹጋላዊው ዋና ዳኛ ጆአኦ ፒንሂሮ ይመሩታል።
ኮፐንሃገን ከ ናፖሊ ፣ ኦሊምፒያኮስ ከ ባየር ሊቨርኩሰን ፣ ሪያል ማድሪድ ከ ሞናኮ ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን ከ ፓሪሰን ዠርማ ፣ ቶተንሃም ከ ቦሩሲያ ዶርትመንድ እንዲሁም ቪያሪያል ከ አያክስ በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።
ማንችስተር ሲቲ የኖርዌውን ክለብ ቦዶ የሚገጥምበት ጨዋታ ምሽት 2:45 ይጀምራል።
በሸዋንግዛው ግርማ