የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 52ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

You are currently viewing የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 52ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

AMN – ጥር 12/2018 ዓ.ም

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 52ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ52ኛው መደበኛ ስብስባ ያሳለፈው ውሳኔ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በሥራ ላይ ያለው የጉምሩክ አዋጅ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ በመሆኑ፣ የአዋጁን ድንጋጌዎች ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር ለማጣጣም፣ በአገራችን እያደገ የመጣውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለመደገፍ፣ እንዲሁም ሕጋዊ ንግድንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ይቻል ዘንድ የማሻሻያ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በማሻሻያ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል አዋጁ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ለኢንቨስትመንት ስለሚሰጥ የታክስና ቀረጥ ማበረታቻ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላላቸውና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው፣ እንዲሁም ከፍተኛ ካፒታል ለሚጠይቁ የኢንቨስትመንት መስኮች በሥራ ላይ የሚውለውን ካፒታል ከግምት ውስጥ የሚያስገባና በአፈጻጸም ላይ የተመሠረተ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል፣ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

3. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ ፖሊሲው በኢንተርፕረነርሽፕ ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ቀጣይነት ኖሯቸው ለሀገራዊ የልማት ግቦች ስኬት ሚናቸውን እንዲወጡ፣ የፈጠራ ባህልን ለማጎልበትና እሴትን ለመጨመር የሚያስችል ምቹ የኢንተርፕረነርሽፕ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት እንዲቻል ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል፣ ፖሊሲው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ከጥር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

ጥር 12 ቀን 2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ

#PMOEthiopia

#Addisababa

#addismedianetwork

#Ethiopia

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review