በትግራይ ክልል የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር የሰነቃቸው ተስፋዎች

You are currently viewing በትግራይ ክልል የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር የሰነቃቸው ተስፋዎች
  • Post category:ፖለቲካ

AMN – ጥር 12/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ከሚገኙ የክልል ባለድርሻ አካላት፣ የፌዴራል ባለድርሻ አካላት እና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ማሰባሰቡ ይታወቃል፡፡

በቅርቡም በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ለመጀመር እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

የትግራይ ክልል ለዓመታት በግጭት ዓውድ ውስጥ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለትግራይ ባለድርሻ አካላት ምን ዓይነት በጎ ውጤቶችን እንደሚያስገኝ መተንተኑ ኮሚሽኑ በክልሉ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ውጤታማ ከማድረጉም በላይ የባለድርሻ አካላትን የነቃ ድጋፍ እና ተሳትፎ እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የሚከተሉት ሀሳቦች ሂደቱ ለትግራይ ባለድርሻ አካላት ብሎም ለመላው ኢትዮጵያዊያን የሚያበረክተውን በጎ አስተዋፅኦ ያብራራሉ፡፡

1. የፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድምፆችን ማሰማት

በዚህ ሂደት እንዲሳተፉ ግብዣ እየቀረበላቸው ያሉ አካላት የተለያዩ አቋሞች እንደሚኖሯቸው ቢጠበቅም በሂደቱ ላይ መሳተፋቸው በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን መብቶች ለማስተጋባት ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል፡፡ የክልሉ ባለድርሻ አካላት ይህን ማድረጋቸው በክልሉ ያለውን እውነታ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖች እንዲገነዘቡ ከማስቻሉም በላይ ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ ለመተለም ይረዳቸዋል፡፡

2. ቀደም ሲል ለተፈፀሙ ጥፋቶች የተጠያቂነት ስርዓትን ማበጀት

ክልሉ የግጭት ቀጠና ውስጥ የቆየ እንደመሆኑና በክልሉ ከፍተኛ እልቂት መከሰቱን ተከትሎ የክልሉ ባለድርሻ አካላት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ጋር በመተባበር ለተፈፀሙ ጥፋቶች የተጠያቂነት ስርዓትን በማበጀት ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የፍትሕ ስርዓት እንዲዘረጋ መደላድሉን ያመቻችላቸዋል፡፡ ይህም መሰል ጥፋቶች ደግመው እንዳይከሰቱ በማድረግ በሀገራችን የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የጋራ መደላድልን በመቀየስ (Common Ground) ሀገራዊ መግባባት የሚሰፍንበትን መንገድ እንዲፈልጉ ያስችላቸዋል፡፡

3. በወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ ባለቤትነትን ማጎልበት

የትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት ልክ እንደሌላው የሀገራችን ሕዝብ ሁሉ በክልላቸው ብሎም በሀገራቸው ዕጣ ፈንታ ላይ ለመነጋገር መፍቀዳቸው በሀገራቸው ላይ የሚኖራቸውን የውሳኔ ሰጪነት ሚና ያዳብራል፡፡ ይህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ በእኩል ደረጃ ባለቤት መሆኑን ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review