ለበረከት ትረፊ ያላት ነፍስ

You are currently viewing ለበረከት ትረፊ ያላት ነፍስ

AMN- ጥር 12/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው የጀርመኖች ቤተ ክርስቲያን ደጅ፣ በየዓመቱ በጥምቀት በዓል ለየት ያለ ትዕይንት ያስተናግዳል።

የቤተክርስቲያኗ አባላት በጥምቀት በዓል በመንገድ ለሚያልፉ ምዕመናን የመጠጥ ውሃ ሲያድሉ ማየት የተለመደ ነው። ይህ በጎ ተግባር ለዓመታት ሲከናወን የቆየ እና ከጀርባው ያለው ታሪክም ጥልቅ የሆነ የእምነት፣ የፍቅር እና የፈውስ ምስክርነት ነው። ለዚህ አገልግሎት መጀመር ምክንያት የሆነው በጀርመን ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰራተኛ የሆነው አቶ እንዳለ ጌታቸው በቅፅል ስሙ “ጃጓር” ተብሎ የሚጠራው ግለሰብ ነው።

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆነው አቶ እንዳለ፣ ከ15 ዓመታት በፊት ታሪኩን የለወጠ አጋጣሚ ገጠመው። ከ15 ዓመታት በፊት በጥምቀት ዋዜማ መንገድ የማስዋብ ሥራ ላይ ሳለ በኤሌክትሪክ አደጋ ክፉኛ ተጎዳ። በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች እና የጀርመን ቤተክርስቲያን አባላት ተረባርበው ወደ ህክምና ወሰዱት።

አቶ እንዳለ በሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ ለፈጣሪው እንዲህ ሲል ተማፀነ፣ “አምላኬ ሆይ! ካዳንከኝ፣ በየዓመቱ በጥምቀት በዓል ለምዕመናን ውሃ አቀርባለሁ!” አምላክ የጃጓርን ጸሎት ሰምቶ ፈውሱን ሰጠው፤ ከሆስፒታል እንደወጣ የመጀመሪያውን ዓመት ውሃ የማጠጣት አገልግሎት በብቸኝነት ጀመረ። በቀጣዩ ዓመት ግን አንድ ለውጥ መጣ፡፡

አገልግሎቱን ለመቀጠል ለቤተ-ክርስቲያኗ ፍቃድ የጠየቀው አቶ እንዳለ፣ የቤተ-ክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎች ጥያቄውን በደስታ ከመቀበል ባለፈ፣ ‘እኛም ከአንተ ጋር ሆነን እናቀርባለን’ እንዳሉት አቶ እንዳለ ይናገራል፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ የጀርመኑ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና አባላት የጃጓርን ስዕለት የራሳቸው አድርገውታል።

የቤተክርስቲያኗ ፓስተር ዮጋን ክላይን ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ ይህ ተግባር የሃይማኖት ልዩነትን ተሻግሮ የሰው ልጅ ለሰው ያለውን ክብርና ፍቅር የሚገልጽበት ትልቅ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ዘንድሮም ይህ አገልግሎት እንደተለመደው በደመቀ ሁኔታ ቀጥሏል። ለአስራ አምስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ መርሐ ግብር፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ጥማቸውን ቆርጠዋል፣ የአብሮነትና የሰላም መልዕክት ተላልፏል።

የቤተክርስቲያኒቱ አመራሮች አገልግሎቱ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ለበረከት ትረፊ ያላት ነፍስ፤ በጃጓር ጉዳት ተነስታ በሺዎች ለሚቆጠሩ ምዕመናን የጥም ውሃ ሆና ፈሰሰች። ይህ ታሪክ የእምነት ልዩነት ሳይገድበው መልካምነትን እንዴት ማስፋት እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review