የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አፈጻጸም መጀመሪያ ከተገመተው በላይ ጠንካራ ሆኖ ተገኝቷል

You are currently viewing የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አፈጻጸም መጀመሪያ ከተገመተው በላይ ጠንካራ ሆኖ ተገኝቷል

AMN ጥር 12/2018

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ከተገመተው በላይ ጠንካራ ሆኖ መገኘቱን በግምገማ መረጋገጡ ተገለጸ።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አፈጻጸም ላይ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነውን አራተኛው የጋራ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ግምገማ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች ውስጥ ሆናም፣ የኢኮኖሚ አፈጻጸሟ መጀመሪያ ላይ ከተገመተው በላይ ጠንካራ ሆኖ መገኘቱ በግምገማው መረጋገጡን ገልጸዋል።

የተቀመጡ የልማት ግቦችም ከታቀደው በላይ መሳካታቸውን የጋራ መግለጫው አመላክቷል።

ለአፈጻጸሙ እውቅና በመስጠት፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የ261 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲለቀቅ መፍቀዱንና ይህም አሁን ባለው ስምምነት መሠረት የሚለቀቀው ጠቅላላ የገንዘብ መጠን ከ2.18 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት የሚከተሉትን ልዩ ድምር ውጤቶችን እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በዚህም መሰረት፦

• ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት፣

• ፈጣን የዋጋ ግሽበት ቅናሽ፣

• የተሻሻለ የበጀት ዲሲፕሊን እና

• የውጭ ምንዛሪ ክምችት በቋሚነት እያደገ መምጣቱን የጋራ መግለጫው አመላክቷል።

እነዚህ ውጤቶች የመደመር መንግሥት ለአጭር ጊዜ መፍትሄዎች ከመገዛት ይልቅ የፖሊሲ አማራጮችን ለመቃኘት፣ ለሀገራዊ የባለቤትነት ስሜት መጎልበት እንዲሁም ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋትና ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ወጥነት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት እንደሚያሳዩም ተገልጿል።

ግልጽ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ስርዓት እና ወደ ገበያ መር ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ጨምሮ በውጭ ምንዛሪ ገበያ ማሻሻያ ላይ የታዩት ዕድገቶች በራስ መተማመንን በመመለስ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ማሻሻል እና የግል ዘርፉን እንቅስቃሴ መደገፍ ያስቻሉ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

በበጀት ረገድ፣ በቅርቡ በተደረጉ የታክስ ፖሊሲ እና የታክስ አስተዳደር ማሻሻያዎች በመታገዝ የመንግሥት ገቢ አሰባሰብ ከሚጠበቀው በላይ መሆኑን በጋራ መግለጫው ተመላክቷል።

በሌላ በኩል ወጪዎች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ኢንቨስትመንቶች እና ለማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ላይ አተኩረው በጥንቃቄ እንዲመሩ መደረጋቸውንም ነው በጋራ መግለጫው የተገለጸው።

መንግሥት የብድር አመላለስ ዘላቂነትን በተመለከተ የታዩ መሻሻሎችንም በበጎ መልኩ መቀበሉም ተጠቁሟል።

ይህም በቡድን 20 (G20) የጋራ ማዕቀፍ ሥር የኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ የመግባቢያ ሰነድ መጠናቀቁን የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።

የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች፤ የገንዘብ ፖሊሲን ለማዘመን፣ የባንክ ቁጥጥርን ለማጠናከር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ገለልተኝነትና አቅም ማሳደግ የሚያስቸሉ ተግባራት መቀጠላቸውም ተጠቁሟል።

የመደመር መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋቱን ወደ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ወደ ግል ኢንቨስትመንት እና ወደ ገቢ ዕድገት ለመለወጥ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ፣ እንዲሁም ሁሉንም አሳታፊ እና ዘላቂ ዕድገትን የሚደግፉ ማሻሻያዎችን ይበልጥ እንደሚያጠናክርም በመግለጫው ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review