በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ፣ በስዊዘርላንድ ዳቮስ-ክሎስተርስ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ኢኮኖሚ ጉባኤ (WEF) ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
ጉባኤው ከጥር 11 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ “የውይይት መንፈስ (The Spirit of Dialogue)” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው።
አቶ አህመድ ሽዴ “የአፍሪካ የሥራ ዕድል ሞተር” በሚል ርዕስ በተካሄደው ከፍተኛ የውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ለአፍሪካ ወጣቶች ሁሉን አቀፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ያለውን ከፍተኛ አቅም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ‘ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም 2.0’ በማንሳት፤ በግብርና እና በምግብ እሴት ሰንሰለት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ በቀላል ማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ከከተማ መስፋፋት ጋር በተያያዙ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።

የሥራ ዕድልን ለማስፋት፣ ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶችን ለማጠናከር እንዲሁም ወጣቶችንና ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማብቃት የሚያገለግለው “ለሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው የ2026 የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና የምርት ስምምነት” እንደ ማዕቀፍ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም “አዲሱ ዓለም አቀፍ የጤና መዋቅር ጅማሮ” በሚል በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ሚኒስትሩ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ ፍትሐዊ፣ አስቀድሞ መተንበይ የሚቻል እና በሀገራት የሚመራ ዓለም አቀፍ የጤና ፋይናንስ ሥርዓት እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ስኬታማ ተሞክሮዎች የጠቀሱ ሲሆን፣ በተለይም በዘላቂ የልማት ግቦች (SDG) አፈጻጸም ፈንድ፣ በጋራ ፋይናንስ ትብብር እና በመድኃኒት ምርት ላይ የተደረጉ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን አንስተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለ’ሉሳካ አጀንዳ’ እና ‘አንድ ዕቅድ፣ አንድ በጀት፣ አንድ ሪፖርት’ ለሚለው መርህ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ በማረጋገጥ፤ በዓለም አቀፍ ጤና ስርዓት ላይ ፍትሐዊነት፣ ትብብር እና የጋራ ኃላፊነት ሊሰፍን እንደሚገባ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ልዑክ በዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ የተለያዩ የባለብዙ ወገን እና የሁለትዮሽ ውይይቶችን እያደረገ ሲሆን፣ አንገብጋቢ ለሆኑ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የጤና ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመፈለግ ከተለያዩ የዓለም መሪዎች ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።