AMN ጥር 13 ቀን 2018 ዓ.ም
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሊግ ምዕራፍ 7ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይከናወናሉ።
በስታድ ቬሎድሮም ኦሊምፒክ ደ ማርሴይ ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ነው።
ሊቨርፑል ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች 12 ነጥብ በመሰብሰብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የመርሲሳይዱ ክለብ ቀጥታ ጥሎ ማለፍ ከሚገቡ ስምንት ቡድኖች አንዱ ለመሆን በዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥቡን ማሳካት ይጠበቅበታል።
ኦሊምፒክ ደ ማርሰይ በአንፃሩ ከውድድሩ ውጪ ላለመሆን ጨዋታው ወሳኝ ነው። የፈረንሳዩ ክለብ በዘጠኝ ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። የሮቤርቶ ዲ ዘርቢ ቡድን ዛሬ ድል ከቀናው ነጥቡን ከሊቨርፑል ጋር እኩል ያደርጋል።
ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የተገናኙት ከ18 ዓመታት በፊት በምድብ ጨዋታ ነበር። በወቅቱ የተደረጉትን የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ሊቨርፑል ማሸነፉ ይታወሳል።
በዛሬው ጨዋታ ሊቨርፑል ሞሐመድ ሳላህን ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ ያገኛል። ጨዋታቸው ምሽት 5 ሰዓት ላይ ይጀመራል።
በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት ቼልሲ ከፓፎስ ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከ ፒ ኤስ ቪ አይንዶቨን ፣ ስላቪያ ፕራግ ከ ባርሰሎና ፣ ጁቬንቱስ ከ ቤኔፊካ ፣ ባየርን ሙኒክ ከ ሴንት ጂልዋስ እንዲሁም አታላንታ ከ አትሌቲክ ቢልባኦ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ጋላታሳራይ ከ አትሌቲኮ ማድሪድ እንዲሁም ካራባግ ከ ፍራንክፈርት ምሽት 2:45 ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።
በሸዋንግዛው ግርማ