AMN- ጥር 14/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ዛሬ በአህጉራችን መዲና አዲስ አበባ፣ ከተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ከመጡ ከንቲባዎች እና ከክልል አስተዳዳሪዎች ጋር ፍሬያማ የአቻ ለአቻ የመማማሪያ መድረክ እያካሄድን እንገኛለን” ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) አማካኝነት በአፍሪካ ከተሞች የፋይናንስ አስተዳደር (Financial Management) አፈፃፀም ላይ በተካሄደው ጥልቅ የዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ አዲስ አበባ ከተመዘነችባቸው 6 መስፈርቶች ውስጥ በ5ቱ የላቀ አፈፃፀም በማስመዝገቧ ልምድ እንድታካፍል ተመርጣለች።
ጥናቱ ከተካሄደባቸው ስድስት የአፍሪካ ከተሞች (ናይሮቢ፣ ዳሬሰላም፣ ሉሳካ፣ ኪጋሊ እና ያውንዴ) መካከል አዲስ አበባ የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ ቀዳሚ መሆን መቻሏን ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው አስፍረዋል።

በተለይም የገቢ እና የፋይናንስ ሀብት አስተዳደርን በማዘመን ረገድ ከተማችን የጀመረችው ሪፎርም ውጤታማና ለአፍሪካ ከተሞች አርአያ መሆኑን የጥናቱ ግኝት አመላክቷል።
ይህ ስኬት፤ ከተማችን ከምትሰበስበው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 71 በመቶውን ለልማት ሥራዎች በመመደብ፣ የዜጎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስናደርግ የቆየነው የሪፎርም ጉዞ ውጤታማነት ማሳያ መሆኑንም ነው ከንቲባ አዳነች የጠቀሱት።
ዛሬ ከተለያዩ ከተሞች ለልምድ ልውውጥ የመጡት ተሳታፊ ከንቲባዎች እነዚህን የሪፎርም ሥራዎች በአካል በመጎብኘት፣ አዲስ አበባ በፋይናንስ እና በገቢዎች ስራ አቅሟን እንዴት ገንብታ ወደ ተግባራዊ ለውጥ እንደቀየረችው ሰፊ ተሞክሮ የምታካፍልም ይሆናል።
መድረኩ የአፍሪካ ከተሞችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ የሚቀርጽበት ታሪካዊ አጋጣሚ ስለመሆኑም ከንቲባ አዳነች ጠቅሰዋል።
ለዚህ ጥናት መሳካትና ለከተማችን እውቅና ለሰጡት ለተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA)፣ እንዲሁም የውጤቱ ባለቤት ለሆኑት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ለሥራ ባልደረቦቻቸው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የላቀ ምስጋናቸውን አቀርበዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ሆና እንደምትቀጥልም ከንቲባዋ ባሰፈሩት መልዕክት ጠቅሰዋል።