AMN ጥር 14 /2018
ኢትዮጵያ እና ቤላሩስ በወታደራዊ ዘርፉ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) እና የቤላሩስ አቻቸው ዲምትሪ ፓንተስ ተፈራርመዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሯ የመግባቢያ ስምምነቱ የኢትዮጵያን ወታደራዊ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ለማሳደግና በወታደራዊ ምርቶች ራሳችንን ለመቻል እየተደረገ ላለው ጥረት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።
ሀገራችንም የአፍሪካ ማዕከል በመሆኗ የጋራ ገበያና ተጠቃሚነትን መፍጠር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተፈራረሙትን ስትራቴጂካዊ ስምምነት ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፥ ሁለቱ ሀገራት የነበራቸውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነትን የሚያጠናክር እንደሆነም ተናግረዋል።
የሁለትዮሽ ስምምነቱ የወዳጅ ሀገራቱን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑም ተገልጿል።
የቤላሩስ የመከላከያ ሚኒስትር ዲምትሪ ፓንተስ በበኩላቸው ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ፣ የመግባቢያ ስምምነቱ የሀገራቱን የቆየ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ብለዋል።
ሁለቱ ወዳጅ ሀገራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ የጠቆሙት ሚኒስትሩ ስምምነቱ በተለያዩ አዳዲስ ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችል ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
የቤላሩስ አየር ሀይል ከነገ ጀምሮ በሚከበረው 90ኛው የኢትዮጵያ የአየር ሀይል የምስረታ በዓል ላይ የአየር ትርኢት እንደሚያቀርቡና ልዑካኑም እንደሚታደሙ ታውቋል።
በዝግጅቱ ላይ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮችን ጨምሮ የቤላሩስ ወታደራዊ ካምፓኒ አመራሮችና የዘርፉ ኤክስፐርቶች እንደተሳተፉ የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን በላከው መረጃ አመልክቷል።