AMN ጥር 14/ 2018 ዓ.ም
የዓለም አቀፍ ወታደራዊ ስፖርት ካውንስል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ኒልቶን ጎሜዝ ሮሊም ፊልሆ ፣ የአፍሪካ ወታደራዊ ስፖርት ፕሬዝዳንት ሜጄር ጄኔራል መኪያኖ አብዱላሂ እና የዓለም አቀፍ ወታደራዊ ስፖርት ዋና ፀሐፊ ሻምበል ሮቤርቶ ሬቺያ ከመቻል ስፖርት ክለብ አመራሮች ጋር በመሆን የአደይ አበባ ስታዲየምን ጎብኝተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ወታደራዊ ስፖርት ካውንስል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ኒልቶን ጎሜዝ ሮሊም ፊልሆ ስታዲየሙ ታላላቅ ውድድሮችን ማስተናገድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የእግር ኳስ መጫወቻ ብቻም ሳይሆን የመዋኛ ገንዳን ጨምሮ የተለያዩ ፋሲሊቲዎችን ያሟላ መሆኑን የተለያዩ የስፖርት አይነቶችን ሊያስተናግድ የሚችል እንደሆነ መገንዘባቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ታላቅ ስታዲየም ሊገነባ በመቻሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል ። የዓለም አቀፍ ወታደራዊ ስፖርት ካውንስል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ኒልቶን ጎሜዝ ሮሊም ፊልሆ ስታዲየሙን ያማረና ድንቅ ሲሉም ገልፀውታል።

ኢትዮጵያ የአለም አቀፉ ወታደራዊ ስፖርት ካውንስል አዲስ አባል በመሆኗ ምስጋና ያቀረቡት ፕሬዝዳንቱ በቀጣዩ ወር ግሪክ ላይ ለሚካሄደው የአገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ ስራ አስፈፃሚ ብርጋዲየር ጄኔራል ኑሩ ሙዘይን በበኩላቸው የአደይ አበባ ስታዲየም የተለየ እና ብቸኛ በመሆኑ አመራሮቹ ይህን በማየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2028 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርባ በመጠባበቅ ላይ እንደምትገኝ የገለፁት ብርጋዲየር ጄነራል ኑሩ ሙዘይን አመራሮቹ በቆይታቸው መቻል ስፖርት ክለብ በስፖርቱ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ፣ለአፍሪካ እና ለአለም ያበረከተውን አስተዋፅኦ እና የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታም በጥልቀት መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ላለፉት ሶስት ቀናት የአፍሪካና የአለም ወታደራዊ ስፖርት አመራሮች ያካሄዱት ጉብኝት የተሳካና ስፖርት ክለቡ ያስቀመጠውን ግብ የመታ እንደነበር መገለጹን የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያሳያል።