AMN – ጥር 14/2018 ዓ.ም
የዓለም ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፉ ቢመጡም፣ ለሕፃናት ነፃነትና ጨዋታ የሚሆኑ የሕዝብ ቦታዎች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበቡ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠነቀቀ። የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኒሴፍ እና ዩኤን-ሀቢታት በጋራ ባወጡት አዲስ መመሪያ፤ መንግሥታትና የከተማ መሪዎች ሕፃናትን የከተማ ፕላን ማዕከል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
መመሪያው ከተሞች ለሕፃናት ደህንነት የተጠበቀ፣ ሁሉንም ያካተተ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራዊ ምክረ-ሐሳቦችን አካትቷል። በተለይም ከተሞች የሚከተሉትን ስድስት መሠረታዊ መርሆች እንዲተገብሩ ያሳስባል፦
• ደህንነቱ የተጠበቀ መሠረተ ልማት፦ የትራፊክ አደጋን የሚቀንሱ ዲዛይኖችና በቂ የመንገድ መብራት ማሟላት።
• የመጫወቻ ዕድሎች፦ በየመንደሩና በመንገዶች ላይ ሕፃናት በነፃነት የሚጫወቱባቸውን ቦታዎች መፍጠር።
• ፍትሐዊ ተደራሽነት፦ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸውና በተጨናነቁ መንደሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሕፃናት ቅድሚያ መስጠት።
• አረንጓዴ ቦታዎች፦ ንጹህ አየር፣ ጥላና ከከፍተኛ ሙቀት የሚከላከሉ ፓርኮችን ማስፋፋት።
• አካታች ዲዛይን፦ አካል ጉዳተኞችንና ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ያገናዘበ ግንባታ።
• ተፈጥሮን ማዕከል ያደረገ ልማት፦ አረንጓዴና የውሃ መሠረተ ልማቶችን በስፋት መተግበር ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ቦታዎች አቅራቢያ የሚኖሩት 44 በመቶ የከተማ ነዋሪዎች ብቻ ሲሆኑ፣ ይህ ቁጥር በታዳጊ ሀገራት ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንደሚል መረጃው ያመለክታል። የአየር ብክለትና የትራፊክ መጨናነቅ የሕፃናትን የመጫወት መብት በከፍተኛ ሁኔታ እየገደቡት መሆኑም በዘገባው ተመላክቷል።
በዓለም ጤና ድርጅት የጤና መወሰኛዎች ዳይሬክተር ዶክተር ኤቲየን ክሩግ እንዳሉት “ደህንነቱ የተጠበቀ የሕዝብ ቦታ ማግኘት የሕፃናት ጤናና ዕድገት መሠረት ከመሆኑም በላይ፣ የማይገሰስ መብታቸው ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2050 ከዓለም ሕዝብ 68 በመቶው በከተሞች ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም አሁኑኑ የሚወሰዱ የፕላን ማሻሻያዎች የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
በአስማረ መኮንን