አረምን ለይቶ የሚያጠፋው ብልሁ ትራክተር

You are currently viewing አረምን ለይቶ የሚያጠፋው ብልሁ ትራክተር

AMN ጥር 15/2018 ዓ.ም

ሰፊ ማሳ ላይ ኬሚካል በጅምላ የመርጨት ዘመን ሊያበቃ ነው? በካናዳ የሚገኙ ገበሬዎች አረምን ብቻ ለይቶ የሚረጭ እና ወጪን የሚቆጥብ የAI ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግብርናውን እየቀየሩት ይገኛሉ።

ጄክ ሌጉዌ በካናዳ ሳስካቸዋን ግዛት ውስጥ የሚኖር የሦስተኛ ትውልድ ገበሬ ነው። አያቱ በ640 ሄክታር መሬት የጀመሩት እርሻ፣ ዛሬ ወደ 17 ሺህ ሄክታር አድጓል። በዚህ ሰፊ ማሳ ላይም ስንዴ፣ ተልባ እና አረንጓዴ ምስር ያመርታል።

ጄክ በልጅነቱ አባቱ እና አያቱ ትራክተር ላይ ተቀምጠው ዘር ሲዘሩ እና ኬሚካል ሲረጩ ለሰዓታት ሲደክሙ ያስታውሳል። “በዚያን ጊዜ ሥራው አድካሚ እና ውጤታማነቱ ዝቅተኛ ነበር” የሚለው ጄክ፣ “ዛሬ ግን ቴክኖሎጂ የምንሠራውን ሥራ በእጅጉ አሻሽሎታል” ይላል።

ጄክ እርሻውን ተወዳዳሪ ለማድረግ በተለይም በኬሚካል ርጭት ረገድ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አስተዋውቋል። ትራክተሩ ላይ የተገጠሙ ሶፍትዌሮች እና የርቀት ካሜራዎች አረሞችን በከፍተኛ ፍጥነት እና ጥራት ለመለየት ይረዱታል።

“ትራክተሩ በሰዓት 15 ማይል እየተጓዘ ሶፍትዌሩ መሬቱን በመቃኘት አረም ባለበት ቦታ ላይ ብቻ ኬሚካል እንዲረጭ ያደርጋል” ሲል ጄክ ያስረዳል።

ይህ ዘዴ ቀደም ሲል ይደረግ እንደነበረው በጅምላ ከመርጨት ይልቅ አረም ባለበት ቦታ ላይ ብቻ በማተኮር የኬሚካል ብክነትን በእጅጉ ይቀንሳል። ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር የጄክ ብቻ ሳይሆን የበርካታ የሰሜን አሜሪካ አርሶ አደሮችም ምርጫ ሆኗል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት 57 በመቶ የሚሆኑት የሰሜን አሜሪካ ገበሬዎች በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ምርታማነትን የሚጨምሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ፍላጎት አላቸው።

አንዳንድ የሰፋፊ እርሻ ባለቤቶችም የምርት መረጃዎችን ለመመዝገብ ዘመናዊ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ሥራቸውን ዲጂታላይዝ አድርገዋል።

እነዚህ መተግበሪያዎች የምርት መጠንን ለማስላት፣ የሚፈለገውን የዘር መጠን ለመተንበይ እና የወደፊት የእርሻ ዕቅዶችን ለማውጣት ያገለግላሉ።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የሚታገዘው የእርሻ ሥራ ለአየር ንብረት ትንበያም በመዋል ላይ ይገኛል። ቴክኖሎጂው የሳተላይት ምስሎችን እና የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ገበሬዎች በማሳቸው ላይ ያለውን ችግር (ለምሳሌ የተባይ ወረርሽኝ) አስቀድመው እንዲያውቁ ያደርጋል።

በግብርናው ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ ያሉት ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሮችን ብቻ ሳይሆን ለሸማቹም ጠቃሚ ሆነው መገኘታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ጄክ ሌጉዌ እንደሚለው ከሆነ ወጣቱ አርሶ አደር ትውልድ ቴክኖሎጂን በደስታ እየተቀበለ ይገኛል። “እርሻን እንደ ንግድ ካየኸው ግሩም የኑሮ ዘዴ ነው፤ እንደ ተራ የኑሮ ዘይቤ ብቻ ካየኸው ግን አስቸጋሪ ይሆንብሃል” ሲል ይደመድማል።

በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምን ዓይነት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተስፋፉ ይሆን? ተሞክሮዎን ያጋሩን።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review