AMN – ጥር 15/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የቅንጅት ሥራዎችን ተቋማዊ በማድረግ በሕግና ሥርዓት የምትመራ መዲናን መፍጠር መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለጸ፡፡
ቢሮው የህግ ማስከበር እና የመልካም አስተዳደር ክላስተር የ6 ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እያካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግረማ፣ ቢሮው የሕግ ማስከበርና የመልካም አስተዳደር ክላስተር 15 ተቋማትን የያዘ መሆኑን ገልፀው፣ በዚህም 11 ግቦችን ይዞ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ባለፉት 6 ወራት ከንግድ ቢሮ ጋር በተሠራው ስራ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ምርትን የሚያከማቹ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ በመዲናዋ የተረጋጋ የግብይት ሥርዓትን መዘርጋት ተችሏልም ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ህገወጥ ነጋዴዎች ምርትን ለማከማቸት እስከ ሸገር ከተማ ድርስ መጋዘኖችን በማዘጋጀት ሥራውን ወስብስበሰ ሲያደርጉ መቆየቱን አንስተው፣ የቅንጅት ሥራውን እስከ ሸገር ከተማ አስተዳደር ከፍ በማድረግ ህገወጦችን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ በሞተር ሳይክሎች ከሚፈፀሙ ስርቆቶች ጋር ተያይዞ ወንጀሎች የሚፈጸሙት ታርጋ በሌላቸው ሞተር ሳይክሎች በመሆኑ ለቁጥጥር አዳጋች እንደነበር ያነሱት ወይዘሮ ሊዲያ፣ ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር በቅንጅት በመስራት ለችግሩ እልባት መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በቅንጅት በተሰሩ ስራዎች በተለያዩ ዘርፎች ውጤት እየተመዘገቡ መሆኑን እና ከሙስና እና ብልሹ አሰራር ጋር ባሉ ጉዳዮች አሁንም አመራሩ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በራሔል አበበ