• “ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ለበለጠ የሀገር ፍቅር ስሜት ያነሳሳል”
ኤልያስ አብዲሳ አጋ
“ጽናትና ጀግንነት አንደበት ኖሯቸው ‘ማንን ትመስላላችሁ?’ ተብለው ቢጠየቁ፤ ደማቸውን ያፈሰሱትን፣ አጥንታቸውን የከሰከሱትን፣ ለሀገር ሉዓላዊነት አይተኬ ሕይወታቸውን የገበሩትን ቀደምት አርበኞቻችንን ይጠቅሳሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተውና ከአራቱም ማዕዘናት ተሰባስበው እንደ አለት በጠነከረው አንድነታቸው አይደለም የሚሞከር የማይታሰብ የማይመስለውን ጭምር በተግባር አድርገው ማሳየታቸው የዓድዋ ድል ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ ይኸን ሽንፈት ለመቀልበስ ኢጣልያ ዳግም ባደረገችው ወረራም የሽንፈት ጽዋ እንድትጎነጭ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ ደማቅ እና አኩሪ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱት መካከል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ አንዱ ናቸው፡፡
ለሀገር እና ለሕዝብ መስዋዕትነት መክፈል ትልቅ ክብርና ዋጋ የሚያሰጥ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ እንደ ሀገር ያለን ልምድ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ደካማ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህንን ክፍተት ለማስተካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ ለአብነት በ2010 ዓ.ም. ከመጣው ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተከታታይነት እየተከወነ የቀጠለው የበጎ ተግባር ሥራ በማሳያነት ይጠቀሳል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በጀት በመመደብ፣ ባለሃብቶችንና ተቋማትን በማስተባበር፣ በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት የተዛመሙ ጎጆዎችን አቃንቶ እና በአዲስ መልክ ሰርቶ ለህብረተሰቡ በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ መስዋዕትነት ከፍለው ሀገራቸውን ከጠላት የጠበቁትንም የዚህ አካል የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የበዓል ቀናትን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ይህ ሲደረግ እየተመለከትን ነው፡፡ በቅርቡ በተከበረው የገና በዓል ላፍቶ በጎነት የመኖሪያ መንደር የቤት ስጦታ ካገኙት መካከል የኮሎኔል አብዲሳ አጋ ልጅ ኤልያስ አብዲሳ አጋ አንዱ መሆናቸው ይኸንኑ በግልጽ የሚያመላክት ነው፡፡ እኛም በመግቢያችን የእኒህን ስመ ጥር አርበኛ ስም የማንሳታችን ምስጢርም ይኸው ነው፡፡
አቶ ኤልያስ በወቅቱ ከአዲስ ሚድያ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ “የኮሎኔል አብዲሳ አጋ ልጅ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ጀግናው አባቴ ከልብ በመነጨ ስሜት ለሀገሩ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ በምላሹም ‘የአብዲሳ አጋ ቤተሰቦች በህይወት አሉ’ ብሎ ከተማ አስተዳደሩ አስታውሶናል፡፡ ለዚህም እኔና ቤተሰቦቼ ታላቅ የደስታ ስሜት ተሰምቶናል” ብለዋል፡፡
“ለበርካታ ዓመታት በቤት ኪራይ አሳልፌአለሁ፡፡ አሁን ያለንበት ወቅትም ኑሮ ትንሽ ከበድ ያለበት ነው። ለሀገር ባለውለታው አባቴ ዘመን ቆጥሮ የተደረገው የቤት ስጦታ ደስታን ከመፍጠሩ ባሻገር ትልቅ እፎይታን ሰጥቶናል፡፡ የቤት ችግር ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ከተማ አስተዳደሩ በመረዳት ካለብኝ የኑሮ ጫና እንድላቀቅ በገና በዓል የቤት ስጦታ ከሙሉ የቤት እቃ ጋር አስረክቦኛል፡፡ የገና በዓልን ከቤተሰቦቼ ጋር አብረን ለማክበር አቅማችን በፈቀደው ልክ ዝግጅት አድርገን፣ የሚበላ የሚጠጣውን አሰናድተን ነበር፡፡ የበለጠ ደስታን ይዞልን የመጣው በዓል የአብዲሳ አጋን ቤተሰብ በህይወት አሉ በማለት ለሀገር የተከፈለውን መሰዋዕትነት ቀን ቆጥሮ እንድንጎበኝ አድርጎናልም” በማለት የተበረከተው የቤት ስጦታ ያለውን ትርጉም አብራርተዋል፡፡
“የቤት ስጦታው ሲሰጠኝ አለቀስኩ። ስሜታዊም ሆንኩ፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ከፈጣሪ ቀጥሎ በእጅጉ አመሰገንኩ፡፡ ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ለበለጠ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚያነሳሳ ተግባርም ነው ለተቀሩት የቤተሰብ አባላቶች ደስታዬን አካፈልኩ ከልቤም ተደሰትኩ” ሲሉ በወቅቱ የተሰማቸውን ስሜት ገልፀዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ትሆን ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋልዓ በተለይም ሰው ተኮር በሆኑ ስራዎች የበርካቶችን ጉድለት ለመሙላት መቻሉን የሚናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር አስራት ንጉሴ ናቸው። ጀግኖቻችንን በህይወት እያሉ ማክበር እና ቤተሰቦቻቸውን መንከባከብ የሀገር አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር ነው፡፡ በዚህም ኮሚሽኑ ላለፉት ሰባት ዓመታት በክረምትና በበጋ የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር ቀርፆ የተለያዩ ተግባራትን ሲከውን እንደቆየም አስታውሰዋል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ ገለፃ፤ በከተማዋ በ2018 በጀት ዓመት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ እና ተግባር በአግባቡ ለመወጣት፣ በክረምት እንዲሁም በበጋው መርሃ ግብር በሚል በሁለት ምዕራፍ በመከፋፈል ሰፊ ስራዎችን ለመስራት ችሏል፡፡ ከእነዚህ ተግባራት መካከል አንዱ የቤት እድሳትና ግንባታ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት ውስጥ ለዜጎች ምቹ በሆነና የከተማዋን ገፅታ በሚገነባ አግባብ ቁጥራቸው 4 ሺህ 990 ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በዚህም ቁጥራቸው 24 ሺህ 950 የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ የሃገር ባለውለታዎች፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው፣ የአልጋ ቁራኛ፣ የአካል ጉዳተኛ እንዲሁም ድጋፍ የሚያሻቸው እጅ አጠር ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ባሉት 4 ሺህ 350 ብሎኮች በህዝብ በተወከሉ አመራሮች አማካኝነት ድጋፍ የሚያሻቸውን ዜጎች በመለየት በቤት ግንባታ፣ በማዕድ ማጋራት፣ በነፃ ህክምና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ የሀገር ባለውለታዎችን ጨምሮ ቁጥራቸው 241 ሺህ 632 ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎች ከአነስተኛ ህክምና እስከ አስተኝቶ የቀዶ ጥገና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው” በሚል የትስስር መርሃ ግብር ባለፉት ስድስት ወራት 65 ሺህ 795 የሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ በዚህም ከሶስት ወር እስከ አንድ ዓመት ትስስር ከተማ አስተዳደሩ ባወጣው መስፈርት መሰረት ወርሃዊ በጀታቸው እንዲሸፈንላቸው ተደርጓል፡፡ ወደ 60 ሺህ 118 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ ቁጥራቸው 1 መቶ 2 መኪና የሚበዛባቸው አካባቢዎች ተለይተው ቁጥራቸው ወደ 10 ሺህ በሚጠጉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተሳለጠ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ከተሳትፎ አንፃር ቁጥራቸው 2 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በተለያየ መርሃ ግብር በድግግሞሽ ተሳትፈዋል፡፡ በመንግስት ወጪ ይሸፈን የነበረን 13 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በበጎ ፍቃደኞች መሸፈን ተችሏል። በዚህም የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ችግር ከማቃለል ባሻገር መንግስት ወደ ሌሎች ልማታዊ አጀንዳዎች ፊቱን እንዲያዞር እድል ስለመፈጠሩ ገልፀዋል፡፡ “የሀገር ባለውለታዎችን ማሰብ፣ ስለሰሩት መልካም ተግባር ጥሩ ምላሽ መስጠት አንድምታው ብዙ ነው” የሚሉት ወይዘሮ አስራት፤ ለሀገር የሚከፈል የትኛውም መስዋዕትነት ጊዜ እና ሰዓትን ቆጥሮ የሚከፍል ነው፡፡ በእርግጥ የትኛውም አካል ለሀገሩ የሆነ ወሳኝ ነገር ሲያደርግ ክፍያ አገኛለሁ በሚል ሳይሆን አንደ አንድ ዜጋ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣትን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በጎ ተግባራት ምላሻቸው መልካም መሆኑን የሚረዳ ትውልድ እንዲፈጠር ከማድረግ አንጻር አሁን ላይ የተጀመሩ ስራዎች እጅግ ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡” የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ ለሀገር ባለውለታዎች ብሎም አቅም ላጠራቸው ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን