የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መርሃ ግብሮች ይደረጋሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የሃሳብ እና መጽሐፍ ውይይት፣ የፎቶ ግራፍ እና የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት (2014 ዓ.ም) እና የሎዛ ድርሳናት (2017 ዓ.ም) ተከታታይ ረጅም ልብ ወለድ መጻሕፍት ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ተመርቀው ለንባብ በቁ፡፡ የመጻሕፍቱ ይዘት በኢትዮጵያ ሚሊኒዬም ዋዜማ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ የሚዳስስ ሲሆን በገጸ ባህሪያቱ ሙግት፣ በፍቅር፣ ባህልን እና ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ ይፈላሰፋል፣ የስደት ገጠመኞችንም ያስቃኛል፡፡ የሎዛ ዘፀአት መፅሐፍ በገፅ 557 እና የሎዛ ድርሳናት በ517 ገፆች የተቀነበቡ ናቸዉ።

የኪነ ጥበብ ምሽት

በነገው ዕለት የግጥም እና ሙዚቃ ምሽት ይካሄዳል፡፡ መርሃ ግብሩ የሚካሄደው ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን ቦታው ከሰአሊተ ምህረት ወደ ወሰን የሚወስደው ዮድ ኢንተርናሽናል ሆቴል ነው ተብሏል፡፡

የሃሳብ ውይይት

በዛሬው ዕለት “የዘመናዊት ኢትዮጵያ ዕውቀት እና ዐዋቂዎች” በሚል ርዕስ የሃሳብና የመጽሐፍት ውይይት ይደረጋል፡  በመርሃ ግብሩ መሰለ ተሬቻ (ዶ/ር) “ተጻራሪ የዕሳቤ ይዞታዎች በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ  የዕውቀት ሥርዓት ግንባታዎች በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንዴት እንደተከናወኑ የሚያሳዩ ሐተታዎች ላይ ሙያዊ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ውይይቱ    ከ8:00 ሰዓት ጀምሮ 4 ኪሎ ኢክላስ ሕንፃ ዋልያ መጻሕፍት አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የስዕል አውደ ርእይ

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓልን አስመልክቶ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የተዘጋጀው የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ነው፡፡ የሰዕል አውደ ርዕዩ የተዘጋጀው በትምህርት ቤቱ የቀድሞ ምሩቃን ሲሆን አውደ ርዕይው  ቅዳሜ ጠዋትን ጨምሮ፣ በሥራ ሰዓትና በሥራ ቀናት ለሁሉም ተመልካች ክፍት መሆኑም ተገልጿል፡፡ አውደ ርዕይው እስከ መጪው የፈረንጆቹ ጥር 30 በእይታ ላይ ይቆያል፡፡

ፊልም

“አቀንቃኙ” የተሰኘው አዲስ ፊልም መታየት ጀመረ፡፡ ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን የተሳተፉበት ይህ ፊልም ሙዚቃዊ ዘውግ ያለው ፊልም ሲሆን ከትናንት ጀምሮ በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች መታየት ጀምሯል፡፡ በፊልሙ ላይ ሰላም ተስፋዬ፣ ሰይፈ ሚካኤል ተስፋዬ፣ ቲና ገብረአምላክ፣ መስከረም አማረና ሌሎችም ታዋቂና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡

የቴአትር መርሃ-ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ። በብሔራዊ ቴአትር ቅዳሜ ከ11፡30 ሰዓት 12ቱ እንግዶች ቴአትር ይታያል። እሁድ ደግሞ በ7፡30 ሰዓት ንጉሥ አርማህ ቴአትር፣ እንዲሁም  እምዩ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር በ11፡30 ሰዓት ላይ ይታያሉ፡፡ በብሔራዊ ቴአትር  በሌሎች ቀናት ደግሞ ሀሙስ 11፡30 ሰዓት  ሸምጋይ እንዲሁም አርብ 11፡30 ሰዓት ዲጊያ ቴአትር  ለእይታ ይበቃሉ፡፡ በሀገር ፍቅር ደግሞ  “የመጨረሻው ፍርድ” ቴአትር  እሁድ  በ11:30 ሰዓት ይታያል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review