• የአዲስ አበባ የብርሃን ዲዛይን በከተማዋ የምሽት ሕይወት ላይ ሥነ- ውበታዊ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ተጠቁሟል
አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቀን ውበቷን ብቻ ሳይሆን በምሽትም እየደመቀች ትገኛለች። በአንድ ወቅት ፀሐይ ስትጠልቅ አብራ የምታንቀላፋው ከተማ፣ ዛሬ ግን በዘመናዊ የብርሃን ዲዛይኖች (Lighting Design) ተውባ ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ አዲስ የኑሮና የተዝናኖት ዘይቤን እያስተዋወቀች ነው።
አዲስ አበባ ቀን ቀን ሰዎች ለሥራ ወዲህ ወዲያ የሚንቀሳቀሱባት፣ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግባትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የምታስተናግድ ከተማ ነች። አሁን ላይ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ በመዲናዋ የምሽት ሕይወትና እንቅስቃሴ ላይ አዳዲስ እሴቶችንና ትዕይንቶችን ጨምራለች። ይህ ትዕይንት በዋናነት የአዲስ አበባ የምሽት የብርሃን ዲዛይን ላይ የተሠሩ ሥራዎች ከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንዲኖራት እያደረጋት ይገኛል። ይህ የብርሃን ዲዛይን የከተማዋን የቀድሞ የምሽት ደብዛዛነት በመግፈፍ ብርሃን ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን፣ በጥቁር ሰሌዳ ላይ በቀለማትና በብርሃን ጨረሮች ሥዕል የመሳል ያህል ትልቅ ሥነ-ውበታዊና ተዝናኖታዊ ፋይዳ ሰጥቷታል። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል የአዲስ አበባ የምሽት ሕይወትና አዳዲስ የብርሃን ዲዛይኖች ከብርሃንነት ባሻገር ምን ዓይነት ሥነ- ውበታዊ (ኤስቴቲክ) ፋይዳ አምጥተዋል ሲል በጨረፍታ ዳስሶታል።
የአዲስ አበባን የምሽት ብርሃን እንደ ሥነ- ውበታዊ ፈጠራ
በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የለሙ መንገዶችና የተለያዩ አገልግሎት በሚሰጡ ንግድ ቤቶች ላይ የሚታየው የብርሃን ዲዛይን ከዚህ ቀደም ከተለመደው በብዙ ረገድ ይለያል። አምፖል በማንጠልጠል ብርሃን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ ለመዲናዋ ሥነ-ውበት ዕድገት ትልቅ ፋይዳ አላቸው። ለዓመታት በነበረን ልምድ በአዲስ አበባ የተገነቡ ግዙፍ ሕንፃዎች በቀን ያላቸው ውበት የሚደነቅ ቢሆንም፣ ምሽት ላይ ግን ደብዝዘው ይታዩ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። አሁን ግን በሕንፃዎቹ ገጽታ ላይ የተሰሩ የምሽት ብርሃን ዲዛይኖች የሕንፃዎቹን ሥነ- ውበታዊ ገጽታ አጉልተው አውጥተዋል። በኮሪደር ልማት የለሙ መንገዶች ላይ የሚታየው የምሽት ገጽታም ብርሃን ከመስጠት ባለፈ፣ የከተማዋ የምሽት እንቅስቃሴ እና የመዝናናት ባህል ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
አዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት የምሽት ሕይወትና እንቅስቃሴ ላይ መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ያለው የብርሃን ዲዛይን፣ ሥነ-ውበታዊና የከተማዋ ገጽታ ላይ መሠረታዊ ለውጦች እያስከተለ ነው ሲል የኪነጥበብ ሃያሲና ደራሲ ዋለልኝ አየለ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው አስተያየት ተናግሯል። አዲስ አበባ ውስጥ ከዚህ ቀደም በጎዳናዎች ላይ የሚሰቀሉ ብርሃኖች ሥነ-ውበታዊ ፋይዳቸውን ታሳቢ በማድረግ ሳይሆን የምሽት ጨለማን ለመግፈፍ በማሰብ ነበር። የተለያዩ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችም አምፖልና ዲም ላይት ከመስቀል ያለፈ የብርሃን ዲዛይን ላይ ይህ ነው የሚባል አረዳድ ነበራቸው ለማለት አያስደፍርም። አሁን ላይ ግን በተለይ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በምሽት የሚታየው የብርሃን ዲዛይን በከተማዋ የምሽት ሕይወት ላይ መሠረታዊ የሆነ ሥነ-ውበታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በየመንገዱ ሰዎች በእግር ሲንሸራሸሩና ክፍት የመዝናኛ ሥፍራዎች ላይ ቁጭ ብለው ሲያወጉ በብዛት መመልከት ከዚህ የብርሃን ዲዛይን መሠረታዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ የመጣ የሕይወት ዘይቤ መሆኑንም አጫውቶናል።

የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ተዘዋውሮ ከጎበኛቸው ሥፍራዎች መካከል አራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ብሔራዊ፣ ስቴዲየምና መስቀል አደባባይ ይገኙበታል። እነዚህ ሥፍራዎች ከዚህ ቀደም ከነበረው የምሽት ገጻቸው ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ አድርገዋል። በብርሃን ዲዛይን አማካኝነት የሕንፃዎች ጠርዞች፣ መስኮቶችና የውጭ ግድግዳዎች በምሽት ጎልተው እንዲታዩ ተደርጓል። ይህም ከተማዋን ግዙፍ የኪነ-ጥበብ ጋለሪ አስመስሏታል። በአንዳንድ ታዋቂ ሕንፃዎች ላይ (ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት) የሚታዩት ተለዋዋጭ ቀለማት ለከተማዋ ተጨማሪ ሥነ-ውበታዊ ገጽታ ሰጥተዋታል። በተለያዩ ቦታዎች በተሰሩ ፋውንቴኖች ላይ የሚታዩ የብርሃን ቀለማት ልውውጦች ደግሞ ተመልካችን የሚያዝናኑና አዕምሮን የሚያድሱ ናቸው፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ የተሠሩ የኮሪደር ልማት መንገዶች ለብርሃን ዲዛይን አዲስ ምዕራፍ በመክፈት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። መንገዶች ከዚህ ቀደም ከነበረው “አምፖል ሰቅሎ ማብራት” ወጥተው፣ አሁን ላይ የራሳቸው የብርሃን ዲዛይን ለውጥ ተደርጎላቸዋል። በእግረኛ መንገዶች ዳር የተተከሉ ዘመናዊ የመብራት ምሰሶዎች እና በመሬት ላይ የተቀበሩ ትናንሽ ብርሃናት (In ground lights) መንገዱን ከመብራት ባለፈ፣ በምሽት ለሚንቀሳቀሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ሌላ ዓይነት የውበት ምልከታ እንዲይዙ አድርገዋል። እንዲሁም በከተማዋ የሚገኙ አደባባዮችና ድልድዮች አሁን ላይ በምሽት የሚለብሱት የብርሃን ካባ፣ አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የምሽት ገጽታ እንዲኖራት እያደረጋት መሆኑን በጉብኝታችን ለመረዳት ችለናል።
ሉሲ አሶሴሽን የተሰኘ ገጸ-ድር በፈረንጆቹ 2022 “The Social and Economic Impact of Urban Lighting” በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ፣ በከተማ ፕላን ውስጥ መብራት በዋነኛነት በሁለት መንገድ እንደሚታይ ጽፏል። አንድም ለደህንነት አንድም ለሥነ- ውበት ፋይዳ (Aesthetic value)። በዚህ ጽሑፍ መሠረት የከተማ የብርሃን ዲዛይን ዓላማው ሕንፃዎችን፣ መንገዶችን እና መዝናኛ ቦታዎችን በሥነ- ውበታዊ መንገድ በማድመቅ የከተማዋን ማንነት መግለጽ እና ሰዎች የተዝናኖት ስሜት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ብሩህ ገጽታ ያለው ከተማ በነዋሪዎች ላይ የመረጋጋትና የደህንነት ስሜት ይፈጥራል። ታዋቂ የሆኑ የኪነ- ሕንፃ ሥራዎች በብርሃን ሲታጀቡ የከተማዋን ታሪክና ጥበብ ለዓለም ያስተዋውቃሉ። እንዲሁም በሚገባ ብርሃን ያገኙ መንገዶች የወንጀል ተጋላጭነትን በመቀነስ ሰዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እንደሚያደርጉ አትቷል።
በእርግጥ ብርሃን በከተማ የምሽት ሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ትልቅ ፋይዳና ትርጉም አለው። በኪነ-ጥበብ ውስጥ የብርሃን ዲዛይን ውበት የሚለካው በዐይን ብቻ ሳይሆን በስሜትም ጭምር ነው። በብርሃን የተዋበች ከተማ ደግሞ በነዋሪዎቿ ላይ የምትፈጥረው ሥነ- ውበታዊና ሥነ- ልቦናዊ እርካታ ከፍተኛ ነው። ለስላሳ እና የተመጣጠነ ብርሃን (Ambient lighting) ባለባቸው አካባቢዎች ሰዎች የመረጋጋትና የመደሰት ስሜት ይሰማቸዋል። ይህ ደግሞ የከተማዋን ነዋሪዎች ከቀን ውጥረት በማላቀቅ የምሽት ዕረፍታቸው የተዋበ እንዲሆን ያደርጋል። እንዲሁም ነዋሪዎች ከተማቸውን በምሽት እንዲህ በብርሃን ተውባ ሲያዩ የተዝናኖት ስሜት ይፈጥርባቸዋል።

እንደ ሃያሲና ደራሲ ዋለልኝ ገለጻ፣ የአዲስ አበባን የብርሃን ዲዛይን ሥነ- ውበታዊ ፋይዳ በተግባር ለማየት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እና የወዳጅነት ፓርክ ጥሩ ማሳያ ናቸው። እነዚህ ሁለት ሥፍራዎች አዲስ አበባ በምሽት ያገኘችውን አዲስ ሥነ- ውበታዊ ዕይታ በጉልህ ያሳያሉ። ፒያሳ እምብርት ላይ የሚገኘው ይኸው መታሰቢያ፣ ምሽት ላይ የሚለብሰው የብርሃን ገጽታ የኢትዮጵያን አሸናፊነትና ክብር በሚያሳይ መልኩ የተነደፈ ነው። የሕንፃውን ግርማ ሞገስ የሚያጎሉና በየተራ የሚቀያየሩ ቀለማት ሕንፃው ልክ እንደ ሕያው አካል እንዲታይ ያደርጉታል። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት በዘመናዊ የብርሃን ቴክኖሎጂ ታጅበው በሕንፃው ላይ ሲፈሱ፣ የታሪክ መዘክርነቱን በዘመናዊ ጥበብ አሳምረውታል። እነዚህ ሥፍራዎች የብርሃን ዲዛይን አንድን የከተማ ክፍል እንዴት ወደ ቱሪስት መስህብነት እንደሚቀይር ትልቅ ማሳያ ናቸው ብሏል።
ሥነ-ውበትን ያጣመረችው “የብርሃን ከተማ” እንደ ማሳያ ዘመናዊ ከተሞች ከብርሃን ጋር ጥብቅ መስተጋብር እንዳላቸው ትልቁ ማሳያ የዓለማችን ተወዳጅዋ ከተማ ፓሪስ ነች። የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ “የብርሃን ከተማ” የሚል ስያሜ ያገኘችው ከዚሁ ከብርሃን አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሆኑን ብሪታኒካ የተሰኘው ገጸ-ድር በፈረንጆቹ ወርሃ ጥር 2026 መጀመሪያ ላይ ባስነበበው “Why Is Paris Called the City of Light?” በተሰኘው ጽሑፍ አስፍሯል። በዚህ ጽሑፍ እንደሰፈረው ፓሪስ ይህን ስያሜ ያገኘችው በሁለት ታሪካዊ ምክንያቶች ነው። አንደኛው በ17ኛው ክፍለ ዘመን በወንጀል ተወጥራ የነበረችውን ከተማ ደህንነቷን ለመጠበቅ በየመንገዱ ፋኖስ በማብራቷ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተደረገው ታላቅ የፍልስፍና እንቅስቃሴ የሆነው የዘመነ-አብርሆት (Enlightenment) የከያኒያንና የምሁራን ማዕከል በመሆኗ ነው። ዛሬ ግን ይህ ስያሜ ሌላ ትርጉም ይዟል። ፓሪስ ብርሃንን የምሽትን ጨለማ ለመግፈፍ ብቻ ሳይሆን እንደ ቀዳሚ የኪነ-ጥበብ መሣሪያ በመጠቀም፣ የምሽት ውበቷን ወደ ላቀ ደረጃ አድርሳለች።
በፓሪስ የብርሃን ዲዛይን ዓላማ ሕንፃዎች በብርሃን ጎልተው እንዲታዩ ብቻ ሳይሆን ሥነ-ውበታዊ ፋይዳቸውና የተዝናኖት እንዲተረጎም ወይም ክሱት እንዲሆን ማስቻል ነው። የፓሪስ የብርሃን ዲዛይነሮች በሕንፃዎች ላይ የሚጥሉት ብርሃን የቀን ብርሃን የማይሰጣቸውን ጥልቀትና ግርማ ሞገስ እንዲላበሱ ያደርጋቸዋል። ለአብነትም ዝነኛው የሉቭር ሙዚየም በምሽት የሚኖረው ወርቃማ ብርሃን፣ የመስታወት ቅርጹንና የውስጥ መዋቅሩን በቀን ከሚታየው በተለየ ሁኔታ ውበቱን ሌላ ገጽታ በመስጠት አጉልቶ ያሳያል። ፓሪስ በብርሃን ዲዛይን ሥራዋ ውስጥ የምትጠቀመው የብርሃን ቀለም “ሞቅ ያለ ነጭ” (Warm White) ነው። ይህ ቀለም የታሪካዊ ሕንፃዎችን ኦሪጅናል የድንጋይ ቀለምና ጥንታዊነት ሳይቀይር፣ ምሽት ላይ ግርማ ሞገስ እንዲላበሱ ያደርጋቸዋል። በተለይ በዓለም ላይ ካሉ ቱሪስቶች አብዛኞቹ ፓሪስን “በምሽት ለማየት” ይመጣሉ። ይህም የከተማዋን ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶችና የምሽት ጉብኝቶችን እጅግ ትርፋማ አድርጓቸዋል። ፓሪስ በብርሃን ዲዛይኗ አማካኝነት በዓለም ላይ “በጣም ማራኪ ከተማ” የሚለውን ስሟን ጠብቃ እንድትቆይ አድርጓታል።
የፓሪስ የብርሃን ዲዛይን ተሞክሮ የሚያስተምረን ብርሃን የቴክኒክ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሥነ-ውበት፣ በቱሪዝምና በምሽት ሕይወት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ነው። አዲስ አበባም አሁን የጀመረችውን የብርሃን ድምቀት ልክ እንደ ፓሪስ፣ ታሪካዊ ሥፍራዎቿንና ዘመናዊ ሕንፃዎቿን በራሳቸው የኢትዮጵያዊነት ቀለም እና ሥነ- ውበታዊ ጥበብ በማስዋብ የምሽት ቱሪዝምን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው የፓሪስ ተሞክሮ ጥሩ ማሳያ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ለከተማዋ ነዋሪዎች የምሽት ሕይወትና እንቅስቃሴ ላይ መሠረታዊ የሥነ- ውበት ብሎም የተዝናኖት ስሜት እየፈጠረና አዲስ የሕይወት ዘይቤ እያስተዋወቀ ይገኛል።
በአብርሃም ገብሬ