አዲስ አበባ በስሟ ልክ እንድትገኝ አያሌ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ ገጽታዋ እየተቀየረ ነው፤ ሰው ተኮር ተግባራት ስጋና ደም ተላብሰው በተግባር እየታዩ ነው፤ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ ነው የሚለውን ከብዙ በጥቂቱ መዘርዘር ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ተግባራት ላይ ደግሞ የዱር እንስሳን በመጠበቅ ለብዝሃ ህይወት መጠበቅ ሚና እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ስራዎችንም በዚያው ልክ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑ አካባቢዎች መካከል እንጦጦ አንዱ ነው፡፡
ወይዘሮ በልግቴ ጩላ ይባላሉ። የእንጦጦ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢው ለ7 ዓመታት ያህል ኖረዋል። ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በአካባቢው የሚገኝ ጅብ ባደረሰባቸው ጥቃት ለአካል ጉዳት ተዳርገው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ወጣት አሸናፊ ተገኑ በበኩሉ፣ “አሁን ላይ ጅቦች ሰዎች በሚንቀሳቀሱባቸው መንገዶች ላይ የመሰባሰብ ባህሪ ይታይባቸዋል፡፡ በፊት ግን በየጫካው ተበታትነው ነበር ይኖሩ የነበሩት” ሲሉ የወይዘሮ በልግቴን ንግግር የሚያጠናክር አስተያየት ለዝግጅት ክፍላችን አጋርቷል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት የደን ሀብት አጠቃቀም ባለሙያ ገዛከኝ ዳምጠው በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት፣ “በክፍለ ከተማው በዋናነት ጅቦች በሰዎች ላይ ጉዳት ሲያስከትሉ ይስተዋላል፡፡ አልፎ አልፎ ጦጣዎች ቤት ውስጥ በመግባት ምግባቸውን የመብላትና እቃ የማጥፋት ነገር ያጋጥማል፡፡ ጃርቶችም የጓሮ አትክልትን ያጠፋሉ” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የስርአተ ምህዳርና ብዝሀ ህይወት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ደመላሽ ተገኝ፣ ጉዳዩን አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍሉ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ ሰዎችና የዱር እንስሳት ሁለቱም ለመኖር የየራሳቸው ፍላጎት አላቸው፡፡ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ድንበር ጥሰው ሰው ወደ እንስሳት፤ እንስሳትም ወደ ሰው ሲያልፉ የሚፈጠር ግጭት የሰው እና የዱር እንስሳት ግጭት በመባል ይጠራል፡፡ በዚህ የተነሳ በሁለቱ አልያም በአንዳቸው ላይ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል፡፡
የዚህ አንደኛው መንስኤ የከተማ መስፋፋት እንደሆነ አቶ ደመላሽ ገልጸዋል፡፡ ይኸንንም ሲያብራሩ፣ “የሰዎች ቁጥር በከተማ ላይ እየበዛ ሲመጣ ደኖች እየተመነጠሩ ወደ መኖሪያ ቤቶች ይቀየራሉ፡፡ የደኖች መመንጠር ደግሞ የዱር እንስሳት ወደተለያዩ ቦታዎች እንዲሰደዱ ያደርጋቸዋል፡፡ በሚሰደዱበት ወቅት በሰው ላይ አደጋ የሚያደርሱበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡
ሌላው ምክንያት የከተማዋ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ነው፡፡ አሁን ላይ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ እየዘመነና እየተሻሻለ ቢመጣም በተወሰነ ደረጃ የእርድ ተረፈ ምርቶች በየአካባቢው ሲጣል ይስተዋላል። ጅቦች ያንን ቆሻሻ ለመመገብ ወደ ከተማ በመግባት ሰው የሚተናኮሉበትና አደጋ የሚያደርሱበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ችግሩ እንደሚከሰት የክትትልና ቁጥጥር ስራው የሚያሳይ ቢሆንም በብዛት የሚከሰትባቸው ግን ደን ባለባቸው በጉለሌ፣ የካ፣ ቦሌ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ናቸው” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የህብረተሰብ አጋርነት ዴስክ ኃላፊ አቶ መዝገበ ስዩምም የአቶ ደመላሽ ሀሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ለዝግጅት ክፍላችን ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም፣ “ለድርጊቱ መከሰት መንስኤው የህዝብ ቁጥር መጨመር ነው፡፡ ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የልማት ስራዎች መስፋፋት በተለይም ፍቃድ በመውሰድም ሆነ በህገ ወጥ መንገድ የኢንቨስትመንት ስራዎች መስፋፋት ነው፡፡ ይህም የዱር እንስሳትን መኖሪያ ይሻማል፡፡ ሌላው መንስኤ ህገ ወጥ ሰፈራ መስፋፋት ነው፡፡ ማህበረሰቡ የዱር እንስሳትን ‘እንደ አጥፊ’ የመመልከት ችግርም ሌላው መንስኤ ነው፡፡ ኋላቀር የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትም እንዲሁ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሚያስከትለው ተጽእኖ እንዴት ያለ ነው?
እንደ አቶ ደመላሽ ገለጻ፤ ጉዳት እየደረሰ ያለው በሰውም በእንስሳቱም ላይ ነው፡፡ ጅብ በሰው ላይ አካል ያጎደለ እና ሕይወት ያሳጣ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡ በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አካባቢ ከ3 እና 4 ዓመታት በፊት ሰዎች ላይ ይኸው አደጋ አጋጥሟል፡፡ ይህም በሰዎች ላይ ስነ ልቦናዊ ጫና አሳድሯል፡፡ እንስሳቱም ላይ ዝርያቸውን የማጥፋት ሙከራዎች ይስተዋላሉ፡፡ እንስሳቱ ሲገደሉ ከብዝሀ ህይወት መመናመን አንጻርም ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡
አቶ መዝገበም ተፅዕኖውን ሲገልጹ፣ “የተፈጥሮ ሀብት እንደ ደን፣ አፈርና ውሃ የመሳሰሉት የመመናመን ችግር ያስከትላል፡፡ ይህም ለአየር ንብረት ለውጥ መዛባት መንስኤ ይሆናል፡፡ አንዱ የዱር እንስሳት ሌላውን የሚበላ ከመሆኑ አንጻር የበይና የተበይን ቁጥር አለመመጣጠን ያስከትላል፡፡ የተበይ ቁጥር እያነሰ ሲሄድ የዱር እንስሳት ወደ ሰው መኖሪያ በመሄድ የቤት እንስሳትን የማጥቃት አልፎ ተርፎም ሰዎች ላይ ጉዳት የማስከተል ችግር ይፈጠራል፡፡ ቦታው እየተመናመነ ሲሄድ የዱር እንስሳት መሰደድና መጥፋት ችግር ያመጣል፡፡ ይህም ከዱር እንስሳት ጉብኝት የሚመጣውን ገቢ ያሳጣል” ብለዋል፡፡
ችግሩን ለመከላከል ምን እየተሰራ ነው?
እንደ አቶ ደመላሽ ገለጻ፤ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በዋናነት ሰዎች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ ነው፡፡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን እንዲያዘምን፣ አጥር እንዲያጥር ማድረግ ላይ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በተጨማሪ ህገ ወጥ የደን መጨፍጨፍ እንዳይኖር በማድረግም እንዲሁ የዱር እንስሳት እንዲጠበቁ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ጉዳቱ በሰውም በእንስሳቱም ላይ በመሆኑ ግጭቱ እንዳይከሰት መከላከል እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ መዝገበ ስዩም በበኩላቸው፣ “የመጀመሪያው ስራ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው። ስለዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ጠቀሜታ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለጥናት ካልሆነ በስተቀር በማታም ይሁን በቀን ወደመኖሪያቸው አለመሄድ እና የድንጋይ ካብ መስራትም ሌላው መፍትሄ ነው፡፡ ችግሩ በከፋበት አካባቢ ደግሞ በኤሌክትሪክ ሽቦ በመታገዝ አካባቢውን ማጠር፣ የምግብ ትርፍራፊ በየቦታው አለመጣልና የማታ እንቅስቃሴዎችን ማስወገድም በተጨማሪ መፍትሄነት የሚያገለግሉ ናቸው” ብለዋል፡፡
የዱር እንስሳት እንደማንኛውን ፍጥረታት ተጠብቀው እንዲኖሩ መብት አላቸው፡፡ በዚህም የዱር እንሰሳት እንዲጠበቁ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ አዋጆችና ደንቦችና ስትራቴጂዎች ወጥተዋል፡፡ እነዚህም የእንስሳቱን ህልውና ከማስቀጠልና ከጥፋት ከመታደግ ባለፈ የእንስሳቱ መጠበቅ ከስነ ምህዳር መጠበቅ አልፎ ተርፎም ለቱሪዝም እንዲውሉ የሚያደረግ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ መዝገበ ገልጸዋል፡፡
በለይላ መሀመድ