ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተፈተነባቸው ጉዳዮች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የስታዲየም እጥረት ነበር። የካፍ (CAF) እና የፊፋ (FIFA) መመዘኛዎችን የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለብ ደረጃ በአህጉራዊ ውድድሮች የሚሳተፉ ቡድኖች ጨዋታቸውን በሞሮኮ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በጎረቤት ሀገራት ለማድረግ ተገድደው ቆይተዋል።
የቅርብ ጊዜ ትውስታን ብንጠቅስ የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ አህጉር የማጣሪያ ጨዋታዎች በምድብ አንድ ከግብጽ፣ ከቡርኪና ፋሶ፣ ከሴራሊዮን፣ ከጊኒ ቢሳው እና ከጂቡቲ ጋር ተደልድላ ማጣሪያዋን ስታደርግ የቆየችው ኢትዮጵያ በራሷ ሜዳ ከማይጫወቱ ሀገራት ውስጥ አንዷ ነበረች፡፡ ይሁንና የብሔራዊ ቡድኑን የ‘ስደት’ ጉዞ ለማብቃት የበርካታ ስታዲየሞች ደረጃ ማሻሻያና የአዳዲስ ስታዲየሞች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ ጽሑፍም፣ የኢትዮጵያ ስታዲየሞች ከነበሩበት ክፍተት ወጥተው ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማለት እያደረጉት ያለውን አስደናቂ ጉዞ እንመለከታለን።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ17ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ጥቅምት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት ባቀረበው ሪፖርት ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ባለመኖሩ ኢትዮጵያ በሜዳ ውስጥና ከሜዳ ውጪ ዋጋ ስትከፍል ቆይታለች፡፡ በ2017 በጀት ዓመት ፌዴሬሽኑ ለወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ በድምሩ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ በቀረበው የፋይናንስ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
መንግስት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወሰዱት እርምጃ በርካታ ስታዲየሞች ዓለም አቀፍ ደረጃን እንዲያሟሉ ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው የማሻሻያ ግንባታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
ለእግር ኳሱ ትኩረት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግስት መፅሐፍ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ “የዛሬ 10 ዓመት የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን ቁመና አኩሪ ምዕራፍ ይቀዳጃል” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል። ለዘመናት የኢትዮጲያን ስም በከፍታ ማስጠራት ያልቻለው የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን ቢበዛ ከ10 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን የሚያኮራበት ጊዜ ይመጣልም ብለዋል፡፡
በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ስታዲየሞች የሲሚንቶና የሳር ክምር መሆናቸው ቀርቶ፣ የፊፋን ጥብቅ መስፈርቶች ለማሟላት በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ዲዛይን እየታደሱ ይገኛሉ። ከአዲሱና ግዙፉ ‘አደይ አበባ’ እስከ ዕድሜ ጠገቡ አዲስ አበባ ስታዲየም፣ ከባህር ዳር እስከ ድሬዳዋ ያሉ ሜዳዎች የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከስደት ለመመለስና የእግር ኳሱ የ‘ስደት’ ጉዞ የሚያበቃበት ተስፋ መታየት ጀምሯል።
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቀደም ሲል ለካፍ ጨዋታዎች እውቅና አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በመቀመጫ፣ በቪአይፒ (VIP) ክፍሎች እና በመጫወቻ ሜዳ ጥራት ምክንያት ታግዶ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት የተሟላ የመቀመጫ ገጠማ እና የሜዳ እንክብካቤ እየተደረገለት ይገኛል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጀመሪያው ምዕራፍ መገንባት የጀመረው በ2004 ዓ.ም ነበር። የስታዲየሙ አጠቃላይ ሥራ ሳይጠናቀቅ ግን በርካታ ስፖርታዊ ውድድሮችን እና ሁነቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከደረጃ መሻሻል ጋር በተያያዘ ውድድሮች እንዳይካሄዱበት በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ታግዶ ቆይቷል። ይህን ተከትሎም ከፍተኛ በጀት ተመድቦ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በሁለተኛ ዙር ማሻሻያዎች ተደርገውለት እና የተለያዩ ተግባራት ሲሰሩለት ቆይቶ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። የቪቪአይፒ፣ ቪአይፒ፣ ፕሪሚየም እና ስታንዳርድ ደረጃ የወጣላቸው 52 ሺህ ወንበሮች የተገጠሙለት ዘመናዊ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ነው።
በቅርቡ ከፍተኛ እድሳት የተደረገለት አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተፈጥሮ ሳር ሜዳው ተቀይሮ በአርቴፊሻል ሳር እንዲተካ ተደርጓል። ይህም ለሀገር ውስጥ ሊግ ጨዋታዎች ትልቅ እፎይታን ሰጥቷል። ድሬዳዋ ስታዲየም እንደዚሁ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው ይህ ስታዲየም፣ የመብራት እና የሜዳ ጥራት ማሻሻያ ተደርጎለት የምሽት ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ሆኗል።
የሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም የዞኑ አስተዳደር ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ግንባታውን በሶስት ምዕራፎች ለማጠናቀቅ ታስቦ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ እየተጠናቀቀ ይገኛል። የእግር ኳስ ሜዳውን ሰው ሰራሽ ሳር የማልበስ፤ ደረጃውን የጠበቀ የመሮጫ መምና የተመልካች መቀመጫን የመግጠም ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው፡፡ የሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ስራው በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ከሚያከናውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚጠቀሰውና የዓለም ዓቀፉን እግር ኳስ ፌዴሬሽን (FIFA) እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ስታንዳርዶችን እንዲያሟላ ተደርጎ በመገንባት ላይ የሚገኘው የአቃቂ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ግንባታን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ የሚገኝ ሌላኛ ስታዲየም ነው፡፡ በስታዲየሙ የፊፋን ስታንዳርድ የሚያሟላ የመጫወቻ ሜዳ ንጣፍ (Hybrid Pitch)፣ የዓለም-ዓቀፉን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስታንዳርድን የሚያሟላ የመሮጫ ትራክ፣ የምሽት ጨዋታዎችን ማድረግ የሚያስችል የመብራት ስርዓት እንዲሁም ሌሎች ዲጂታል ስርዓቶችን ለመተግበር የሚያስችል ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂኒየር አያልነሽ ሐብተማርያም የተመራና የአዲስ አበባ ስፖርት ቢሮን ጨምሮ የስራ ተቋራጩ ኤምኤንአርሲ፣ ዚያስ ኢንተርናሽናል ዲዛይንስ እንዲሁም በአውሮፓ ስቴዲየሞች ላይ ሰፊ ልምድ ያካበተው የጣሊያኑ ሊሞንታ የተሳተፉበት ውይይት ከሰሞኑን ተካሂዷል፡፡ የሜዳ ንጣፍ ስራው የአዲስ አበባን የአየር ንብረት ከግምት ያስገባና ፊፋ የሚያስቀምጣቸውን ደረጃዎች የሚያሟላ ይሆን ዘንድ የተሻለውን ግብዓት ለመምረጥ የሚያስችል ውይይት ስለመደረጉም ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ እንደ ትልቅ የስኬት ምዕራፍ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ሌላኛው ስራ የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ መጠናቀቅ ይሆናል። ከሰሞኑም ዋናው የመጫወቻ ሜዳ በፊፋ ተገምግሞ እውቅና አግኝቷል። የመጫወቻ ሜዳው የተለያዩ መመዘኛዎችን በከፍተኛ ውጤት በማለፉ ነው እውቅና የተሰጠው። ይህ ስታዲየም ከ60 ሺህ በላይ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በካፍ ካታጎሪ 4 (ከፍተኛው ደረጃ) እንዲመደብ ታስቦ የተሰራ ነው። ስታዲየሙ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎች፣ የጋዜጠኞች ማዕከል፣ የተጫዋቾች መቀየሪያ ክፍሎች እና የቪአይፒ አገልግሎቶችን የያዘ በመሆኑ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎችን የማስተናገድ ሙሉ አቅም አለው። በቅርቡ በተደረጉ ግምገማዎች መሠረት፣ ስታዲየሙ የቀሩት ጥቂት የማጠናቀቂያ ስራዎች (እንደ መቀመጫ ገጠማ እና የድምጽ ስርዓት) እንደተጠናቀቁ ለታላላቅ ጨዋታዎች ክፍት እንደሚሆን ይጠበቃል።
እነዚህ ስታዲየሞች በሙሉ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ፣ ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም ይኖራታል። የስታዲየሞች ጥራት መሻሻል በቀጥታ ከውጤት ጋር ይገናኛል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በገዛ ሜዳው እና በደጋፊው ፊት መጫወቱ ያለውን የስነ-ልቦና የበላይነት በገንዘብ የሚተመን አይደለም። በተጨማሪም፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች መኖራቸው ሀገሪቱ የአፍሪካ ዋንጫን (AFCON) ለማስተናገድ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ መሰረት ነው።
በሳህሉ ብርሃኑ